ውዱእና ከቆሻሻ መጸዳዳት፣ ትሩፋት የሚያስገኙና የላቁ ተግባራት ናቸው፡፡ አንድ ባሪያ ዓላማውን ካሳመረና ለአላህ ካጠራ፣ እንዲሁም ከአላህ ምንዳን ከከጀለበት፣ አላህ በርሱ ወንጀሉንና ስህተቱን ያብስለታል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡-«አንድ ሙስሊም ባሪያ ውዱእ በሚያደርግበት ጊዜ፡ ፊቱን ሲታጠብ፣ በዓይኑ በመመልከት የሰራው የእይታ ወንጀል ከውሃው ጋር ከፊቱ ይወገዳል፡፡ እጁን ሲታጠብ፣ በእጁ የፈፀመው ወንጀል ከውሃው ጋር ይወገዳል፡፡ እግሮቹን ሲያጥብ፣ በእግሮቹ በመጓዝ የፈፀመው ወንጀል ከውሃው ጋር ከእግሮቹ ይወገዳል፡፡ በዚህ መልኩ ከወንጀል ጽዱዕ ሆኖ ይወጣል፡፡» ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 244) |
ውዱዕ የማደርገው እንዴት ነው? ትንሹን ሐደስ የማስወግደውስ?
አንድ ሙሰሊም ውዱእ ማድረግ በሚፈልግ ጊዜ ውዱዕ ማድረጉን ሊያስብ ይገባል፡፡ ይኸውም በልቦናው ሐደስን እንደሚያስወግድ ማሰብ ነው፡፡ በልብ ማሰብ (ኒያ) ለማንኛውም ተግባር ተቀባይነት መስፈርት ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡ - «ስራዎች የሚለኩት እንደ ታሰበላቸው ዓላማ ነው፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 1/ ሙስሊም 1907) ከዚያም በሚከተለው ቅደም ተከተል መሰረት እንዲሁም በማዕዘናቱ መሐከል ረዥም ቆይታ ሳይኖር ወዱእ ማድረግ ይጀምራል፡፡


በአላህ ስም (ቢስሚላህ) ይላል፡፡

መዳፎቹን ሶስት ጊዜ ይታጠባል፡፡ ይህ የተወደደ ተግባር(ሙስተሐብ) ነው፡፡

በውሃ ይጉመጠመጣል፡፡ ይኸውም በአፉ ውስጥ ውሃን በማስገባትና ተግሞጥሙጦ በመትፋት ይሆናል፡፡ ይህን ሶስት ጊዜ ቢያደርግ የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ማድረግ ነው፡፡

ይሰረነቃል፡፡ ይኸውም ውሃን በአፍንጫው በመሳብ ከዚያም በአፍንጫ ገፍቶ ማውጣት ነው፡፡ ውሃውን የሚያስወጣው በአፍንጫው በሚያስወጣው አየር ነው፡፡ በርሱ ላይ ጉዳት ከሌለው በስተቀር ውሃን በሚገባ ወደ ውስጥ መሳብ (መሰርነቅ) የተወደደ ነው፡፡ ሶስት ጊዜ ይህን ማድረግ ምስተሐብ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ፊቱን ይታጠባል፡፡ ከግንባሩ፣ ከፀጉር መብቀያው ጫፍ እስከ አገጩ ስር ድረስ፣እንዲሁም ከአንዱ ጆሮ እስከ ሌላኛው ጆሮ ድረስ በመታጠብ የሚፈፀም ነው፡፡ ይህንንም ሶስት ጊዜ ቢፈፅም የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ግዜ ብቻ ነው፡፡ ጆሮዎች የፊት አካል አይደሉም፡፡

እጆቹን ከጣቶቹ ጫፍ እስከ ክርኑ ድረስ ያጥባል፡፡ ክርኖች በትጥበቱ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ሶስት ጊዜ መደጋገሙ ይወደዳል፡፡ ግዴታው አንድ ግዜ ብቻ ነው፡፡

እራሱን(ፀጉሩን) ያብሳል፡፡ ይኸውም መዳፎቹን በውሃ በማራስ፣ ከግንባሩ በመጀመር፣ ከማጅራቱ ቀጥሎ እስከለው የኋለኛው የራስ ጫፍ ድረስ ማበስ ነው፡፡ በመዳፎቹ እያበሰ ወደ ፊትለፊት መመለሱ ይወደዳል፡፡ እንደሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች ሶስት ጊዜ መደጋገም የተወደደ አይደለም፡፡

ጆሮዎቹን ያብሳል፡፡ ይኸውም ጭንቅላቱን ካበሰ በኋላ ሁለቱን አመልካች ጣቶቹን ጆሮዎቹ ውስጥ በማስገባት በአውራጣቱ ደግሞ የላይኛውን የጆሮው ክፍል ማበስ ነው፡፡

እግሮቹን ከነቁርጭምጭሚቶቹ ያጥባል፡፡ ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ማድረጉ የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ካልሲ ከለበሰ መስፈርቶቹን ጠብቆ በላዩ ላይ ማበስ ይችላል፡፡ (ገጽ፣ 97 ተመልከት)
ትልቁ ሐደስ(ምናባዊ ቆሻሻ) እና ትጥበቱ
ትጥበትን ግድ የሚያደርጉ ነገሮች
እነኚህ ነገሮች፣ አንድ ሙስሊም ከተገበራቸው ሠላትን ከመስገድና ጠዋፍ ከማድረግ በፊት ገላውን መታጠብ ግዴታ የሚያድርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ ሰው ከመታጠቡ በፊት ትልቁ ሐደስ አለበት ይባላል፡፡
ትጥበትን ግድ የሚያደርጉ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡
1
የፍቶት ፈሳሽ (የዘር ፍሬ - መኒይ)፣ በንቃት ሕሊናውም ሆነ በእንቅልፍ ውስጥ፣ በእርካታ መልክ እየተገፋተረ መውጣት፡፡
የፍቶት ፈሳሽ (መኒይ) የሚባለው በጣም በስሜት ውስጥ ሲገባና እርካታ ሲሰማ ከብልት የሚወጣ ነጭና ትኩስ ፈሳሽ ነው፡፡
2
የግብረ ስጋ ግንኙነት፡ ይህ የፍቶት ፈሳሽ (መኒይ) ባይፈስም፣ የወንድ ብልት ብቻ የሚጠቁም ድርጊት ነው፡፡ የወንዱ ብልት ጫፍ ሴቷ ብልት ውስጥ መግባቱ ብቻ ትጥበትን ግዴታ ያደርጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡-«(ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት ጀናባ) ብትኾኑ (ገላችሁን ) ታጠቡ፡፡» ይላል፡፡ (አል ማኢዳ 6)
3
የወር አበባና የወሊድ ደም መፍሰስ
- የወር አበባ ደም የሚባለው፣ በየወሩ ሴቶች የሚፈሳቸው ተፈጥሯዊ ደም ነው፡፡ ሰባት ቀን ወይም ከዚያ በላይ ይፈሳል፡፡ እንደሴቶቹ ተፈጥሯዊ ልዩነት ከዚያም ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡
- የወሊድ ደም ደግሞ በመውለዳቸው ምክንያት ከሴቶች የሚወጣ ደም ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡
የወር አበባና የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች፣ ደሙ በሚፈስባቸው ቀናት የጾምና የሠላት ግዴታ ይነሳላቸዋል፡፡ ከደሙ ሲጸዱ፣ ጾሙን ይከፍላሉ ሠላቱን ግን አይከፍሉም፡፡ በነኚህ ቀናት ውስጥ ባሎቻቸው ሊገናኟቸው አይፈቀድላቸውም፡፡ ከግንኙነት መለስ ባለ ነገር ግን መጠቃቀምና መደሰት ይችላሉ፡፡ ሴቶቹ ደሙ ከቆመላቸው በኋላ ገላቸውን መታጠባቸው የግድ ይሆናል፡፡
አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹህ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቧቸው፡፡ ንጹህ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኟቸው፡፡» ይላል፡፡ (አል በቀራ 222) «ንጹህ በኾኑም ጊዜ » ማለት ገላቸውን በታጠቡ ጊዜ ማለት ነው፡፡

ለግዴታ ትጥበት ሰውነትን በጠቅላላ በውሃ ማዳረስ በቂ ነው፡፡
አንድ ሙስሊም ከጀናባ ወይም ከትልቁ ሐደስ የሚጠራው እንዴት ነው?
አንድ ሙስሊም መጽዳትን በልቡ አስቦ ገላውን በሙሉ በውሃ ከታጠበ፣ ከትልቁ ሐደስ ይጸዳል፡፡
- ይህ ትጥበት የተሟላ የሚኾነው ግን፣ ከተጸዳዳ በኋላ የሚያደርገውን ዓይነት ኢስቲንጃ አድርጎ፣ውዱእን አስከትሎ፣ከዚያም ሰውነቱን በጠቅላላ በውሃ አዳርሶ ሲታጠብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ትጥበት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአስተጣጠብ ፈለግ ጋር ስለሚገጣጠም ከምንዳ አንፃር ከፍተኛው ነው፡፡
- አንድ ሙስሊም ከጀናባ ሲታጠብ ትጥበቱ ከውዱእ ያብቃቃዋል፡፡ ከትጥበቱ በተጨማሪ ውዱእ ማድረግን አይገደድም፡፡ በላጩ ግን፣ በነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) የአስተጣጠብ ፈለግ መሰረት ወዱእንም ያካተተ ትጥበት መታጠብ ነው፡፡
ከኢስላም ገርነት መገለጫዎች መካከል አንድ ሙስሊም ወዱእ ሲያደርግ በውሃ በራሰ መዳፉ እግሮቹን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነውን የላይኛውን የካልሲውን ወይም የጫማውን ክፍል እግሮቹን በመታጠብ ምትክ ማበስ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን፣ ቀደም ሲል ውዱእ እያለው ያጠለቃቸው ወይም የተጫማቸው መሆን አለበት፡፡ ሳያወልቅ ሊያብስ የሚችለው ደግሞ፣ ነዋሪ ከሆነ ከ24 ሰዓታት ላልበለጠ ጊዜ ሲሆን መንገደኛ ከሆነ ደግሞ ለ72 ሰዓታት ያህል ነው፡፡
ከጀናባ ለመጽዳት በሚያደርገው ትጥበት ግን በፈለገው ሁኔታ ላይ ቢሆንም ሁለቱን እግሮችን ማጠብ ግዴታ ነው፡፡

ውሃን መጠቀም ያቃተው ወይም ያልቻለ ሰው
አንድ ሙስሊም በበሽታ፣ ውሃ በማጣት፣ ወይም ለመጠጥ ብቻ እንጂ ውሃ የማያገኝ በመሆኑ ምክንያት ውዱእ ለማድረግ ወይም ሰውነቱን ለመታጠብ ውሃን መጠቀም ካልቻለ አለያም ካቃተው፣ ውሃ አግኝቶ መጠቀም እስከሚችል ድረስ በአፈር ተየሙም ማድረግ ይፈቀድለታል፡፡
የተየሙም አደራረግ፡ በውስጠኛው መዳፎቹ አፈር ላይ አንድ ምት በመምታት በመዳፎቹ ላይ በቀረው አፈር ፊቱን ማበስ፣ቀጥሎም የቀኝ እጁን የላይኛውን የመዳፍ ክፍል በግራው የውስጠኛ መዳፍ ማበስ፣ እንዲሁም የግራ እጁን የላይኛውን የመዳፍ ክፍል በቀኙ የውስጠኛ መዳፍ በማበስ ይፈፅማል፡፡
