ከነጃሳ(ግልፅ ቆሻሻ) መጥራት

ከነጃሳ(ግልፅ ቆሻሻ) መጥራት


  • ነጃሳ ማለት፣አምልኮ ስንፈፅም ኢስላላማዊው ድንጋጌ በቆሻሻነት የፈረጃቸውንና ከነርሱ እንድንጠራ ትዕዛዝ የሰጠበትን ተጨባጭ ነገሮች የሚገልፅ ነው፡፡
  • ነገሮች መሰረታቸው የተፈቀደና ንጹህ ነው፡፡ ነጃሳ ባዕድና በአጋጣሚ የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የአንድን ልብስ ንጹህነት ከተጠራጠርንና ነጃሳ እንደተገኘበት እርግጠኞች መሆን ካልቻልን፣ በመሰረቱ ንጹህ ነው እንላለን፡፡
  • ሠላት ለመስገድ ስንፈልግ ሰውነታችንን፣ ልብሳችንና የምንሰግድበትን ስፍራ ከነጃሳ ነገሮች የማጽዳት ግዴታ አለብን፡፡

ነጃሳ ነገሮች


1 የሰው ልጅ ሽንትና ዓይነ ምድሩ
2 ደም፤ ትንሽ ጠብታ ደም ግን ችግር የለውም
3 ስጋቸው የማይበላ የማንኛውም እንሰሳት ሽንትና ፋንድያ (ገጽ 183 ተመልከት)
4 ውሻና አሳማ
5 ሙት እንሰሳት (የሞቱ እንሰሳትን ሁሉ የሚመለከት ሲሆን ስጋቸው የሚበላና በሸሪዓዊ መንገድ የታረዱትን ግን አይመለከትም፡፡ ገጽ 184 ይመልከቱ ) የሞተ ሰው አካል ፤አሳና ነፍሳቶች ቢሞቱም ንጹህ ናቸው፡፡



ከነጃሳ መጽዳት


ነጃሳ(ግልፅ ቆሻሻ) ከሰውነት፣ ከልብስ ወይም ከአንድ ቦታ፣ ወዘተ. ላይ ሲታጠብ፣አወጋገዱ፣ ውሃን ወይም ሌላን ነገር በመጠቀም፣ አለያም በሌላ መንገድ ቢሆንም፣ የነጃሳው ነገር መልኩና አካሉ ከቆሸሸው ቦታ ላይ መወገዱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢስላማዊው ድንጋጌ ነጃሳን ማስወገድን እንጂ ከውሻ ነጃሳ በስተቀር ነጃሳን ለማስወገድ በተወሰነ ቁጥር ማጠብን መስፈርት አላደረገም፡፡ የውሻ ነጃሳም ቢሆን ልጋጉን፣ሽንቱንና ዓይነ-ምድሩን እንጂ አካሉን አያካትትም፡፡ የውሻን ቆሻሻ በተመለከተ፣የመጀመሪያውን በአፈር አድርጎ፣ ሰባት ጊዜ ማጠብን አዟል፡፡ የተቀሩትን ነጃሳዎች ግን መልካቸውና አካላቸው መወገዱ ብቻ በቂ ነው፡፡ የመልኩ ፋና እና ሽታው መቅረቱ ችግር አይኖረውም፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የወር አበባ ደምን በማጠብ ዙሪያ ለአንዲትን ሠሓቢት፡- «ደሙን ማጠብሽ ይበቃሻል ፋናው መቅረቱ ችግር የለውም፡፡» ብለዋታል፡፡ (አቡ ዳውድ 365)




የኢስቲንጃእ(ሀፍረተ ገላንና አካባቢውን ማጠብ) እና የመጸዳዳት ስርዓት


  • አንድ ሰው ሽንት ቤት ሲገባ፣ ግራ እግሩን ማስቀደምና ‹‹ቢስሚላህ፣አላሁመ ኢኒ አዑዙ ቢከ ሚነል ኹቡሲ ወል ኸባኢስ›› - በአላህ ስም፣ አምላኬ ሆይ ከእርኩሱና ከእርኩሲቷ (ሰይጣን) በአንተ እጠበቃለሁ- ማለቱ ይወደዳል፡፡
  • በሚወጣ ጊዜ ደግሞ ቀኝ እግርን በማስቀደም ‹‹ጉፍራነከ›› -ምህረትህን ለግሰን- ማለት ይወደዳል፡፡
  • በሚጸዳዳበት ጊዜ ሀፍረተ ገላውን ከሰዎች እይታ የመከለል ግዴታ አለበት፡፡
  • ሰዎች በቆሻሻው በሚጎዱበት ስፍራ መጸዳዳት ክልክል ነው፡፡
  • የሚጸዳዳው ከቤት ውጭ ባለ መስክ ውስጥ ከሆነ፣ እርሱ ሊጎዳቸው፣ እነሱም ሊጎዱት የሚችሉ እንሰሳት አለያም አውሬዎች የሚኖሩበት በሆነ ጎሬ ውስጥ መጸዳዳቱም ክልክል ነው፡፡
  • የሚጸዳዳው በሜዳ ላይ ከሆነና የሚከልለው ግርዶሽ የሌለ ከሆነ፣ ፊቱን ወደ ቂብላ ማዞር ወይም ለቂብላ ጀርባውን መስጠት አይገባውም፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «በምትጸዳዱበት ጊዜ፣ ስትሸኑም ሆነ ዓይነምድር ስታስወግዱ፣ፊታችሁን ወደ ቂብላ አታዙሩ ጀርባችሁንም ለቂብላ አትስጡ፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 386/ ሙስሊም 264)
  • የሚፈናጠሩና የሚረጩ ነጃሳዎች ልብሱና ሰውነቱን እንዳይነኩት ጥንቃቄ ማድረግ፣ከነኩት ደግሞ የማጠብ ግዴታ አለበት፡፡
  • ተጸዳድቶ ሲያበቃ ከሁለት አንድ ነገር መፈፀም አለበት


      • የሽንትና የዓይነምድር መውጫ አካሎቹን በውሃ ማጠብ (ኢስቲንጃእ)

      • ወይም

        በሶስት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ደንጋዮች፣ለስላሳ የመጸዳጃ ወረቀቶች፣ ወይም ሰውነቱን ከነጃሳ ሊያጸዳለት በሚችል መሰል ነገር ማጽዳት ነው፡፡