አላህ ሱ.ወ፣ በበርካታ ዓለማዊና መንፈሳዊ ምክንያቶች ጾምን ግዴታ አድርጓል፡፡ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል
1
የአላህን ፍራቻ ማጽናት
ጾም፣አንድ ባሪያ የሚወዳቸውን ነገሮች ወይም ፍላጎቶቹን በመተው፣ ስሜቱን በመጫን፣ አላህን የሚገዛበት አምልኮ በመሆኑ፣ በሁሉም ስፍራና ወቅት፣ በድብቅም ሆነ በይፋ ነፍሱን በአላህ ፍራቻ እንዲያንጽና የአላህን ምርመራ እንዲያስተነትን ያደርገዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡›› ብሏል (አል በቀራ 183)
2
ከወንጀልና ከሃጢኣት በመራቅ ላይ ስልጠና ወይም ልምምድ መስጠት
አንድ ጾመኛ ሐላል ነገሮችን በመከልከል የአላህን ትዕዛዝ ማክበር ከቻለ፣ የወንጀልና የሀጢኣት ስሜቱን በመለጎሙና አላህ ከገደበው ወሰን በመጠበቁ፣ በስህተት ላይ ባለመዘወተር የበለጠ ቻይ ይሆናል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የሐሰት ንግግርንና በሱም መሥራትን ያልተወ ሰው፣ አላህ (ሱ.ወ) ምግብና መጠጡን ከመተዉ ጉዳይ የለውም፡፡›› (አል ቡኻሪ 1804) ውሸት ማውራትና በውሸት መሥራት ያልተወ ሰው፣ ለጾም የተደነገገለትን ዓላማ በስራ ላይ አላዋለም ማለት ነው፡፡
3
ችግረኞችን ማስታወስና መደገፍ
ጾም፣ የተራቡና የተቸገሩ ሰዎችን ሕይወት የሚካፈሉበትና ዓመቱን ሙሉ በችግርና በሰቆቃ የሚያሳልፉትን ድሆች ሁኔታ የሚያስታውሱበት የአምልኮ ዘርፍ ነው፡፡ ትክክለኛ የአላህ ባሪያ፣ ድሃ ወንድሞቹ ምን ያህል በረሃብና በጥማት እንደሚቸገሩ ያስታውሳል፤ በመሆኑም ለነርሱ የእርዳታ እጁን በመዘርጋት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡

ጾመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት፡- ጾሙን ሲፈታና ፈጣሪውን ሲገናኝ ይደሰታል፡፡