የጾም ትሩፋት

የጾም ትሩፋት


ጾም በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉ በርካታ ትሩፋቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

1

በአላህ አምኖ፣ ትዕዛዙንም አክብሮ፣ በረመዳን ትሩፋት ዙሪያ የተላለፉ ጉዳዮችን እውነት ብሎ ተቀብሎ እንዲሁም አላህ ዘንድ የሚያገኘውን ምንዳ በመከጀል ረመዳንን የጾመ፣ ቀደም ሲል የሰራው ወንጀሉ ይማርለታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ረመዳንን፣ በአላህ አምኖ የሚያስገኝለትን ምንዳ አስቦና ከጅሎ የጾመ ሰው ቀደም ሲል የሰራው ወንጀል ይማርለታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1910 / ሙስሊም 760)

2

ጾመኛ፣ ከአላህ ጋር ሲገናኝ በመጾሙ ምክንያት በሚያገኘው ላቅ ያለ ምንዳና ጸጋ ይደሰታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ጾመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት፡፡ በሚያፈጥርበት ጊዜ የሚደሰተውና ከጌታው ጋር ሲገናኝ የሚደሰተው ደስታ ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 1805 /ሙስሊም 1151)

3

በጀነት ውስጥ ከጾመኞች በስተቀር ማንም የማይገባበት የሆነ ረያን የሚባል በር አለ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በጀነት ውስጥ ረያን የሚባል በር አለ፡፡ የትንሳኤ ቀን ጾመኞች ይገቡበታል፡፡ ከነርሱ ሌላ ማንም በርሱ በኩል አይገባም፡፡ የት አሉ ጾመኞች? ይባላል፡፡ ወዲያውም እነሱ ወደርሱ ይነሳሉ፡፡ ከነርሱ ሌላ ማንም በርሱ በኩል አይገባም፡፡ እነሱ ገብተው ሲያበቁ ይዘጋል፡፡ ማንም በሱ በኩል አይገባም፡፡›› (አል ቡኻሪ 1797/ ሙስሊም 1152)

4

አላህ (ሱ.ወ) የጾምን ምንዳ ወደራሱ አስጠግቶታል፡፡ እናም ክፍያውና ምንዳው፣ ከቸሩ፣ ከለጋሱና ከኃያሉ ጌታ ዘንድ የሆነለት ሰው ሊደሰት ይገባል፡፡ አላህ ባዘጋጀለትም ሽልማት ይበሰር፡፡ አላህ (ሰ.ወ) በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንደበት ሲነግረን፡- ‹‹ፆም ሲቀር ሁሉም የአደም ልጆች ስራ ለራሳቸው ነው፤ እርሱ ግን የኔ ነው ምንዳውን የምከፍለው እኔው ነኝ፡፡›› ይላል፡፡ (አል ቡኻሪ 1805 /ሙስሊም 1151)