የረመዳን ጾም

የረመዳን ጾም

የጾም ትርጉም


ጾም በኢስላም ያለው ትርጉም፡ ጎሕ ከቀደደበት ሰዓት ጀምሮ፣ ፀሐይ እስክትጠልቅ (የመግሪብ ሠላት አዛን የሚባልበት ወቅት) ድረስ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከግብረ ስጋ ግንኙነትና ከሌሎችም ጾምን ከሚያበላሹ ነገሮች እራስን በመቆጠብና በማገድ አላህን መገዛት ነው፡፡


የረመዳን ወር በላጭነት


የረመዳን ወር፣ በኢስላማዊው ቀመር ዘጠነኛው ወር ነው፡፡ ረመዳን ከዓመቱ ወራት ሁሉ በላጩ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከተቀሩት ወራት በበርካታ ነገሮች አልቆታል፡፡ ከነዚህ ብልጫዎች መካከል የሚከለተሉት ይገኙበታል፡፡

1

አላህ (ሱ.ወ) የተከበረውንና እጅግ የላቀውን መጽሐፍ -ቁርኣንን- በውስጡ በማውረድ የመረጠው ወር ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡፡-‹‹(እንድትጾሙ የተፃፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ፣ ከቅን መንገድና (ውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲሆን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ ከናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፡፡›› (አል በቀራ 185)

2

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ረመዳን ሲገባ የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ የጀሀነም በሮች ይዘጋሉ፤ ሰይጣናት ይታሰራሉ፡፡›› (አል ቡኻሪ 3103/ ሙስሊም 1079) አላህ (ሱ.ወ) መልካምን በመሥራትና ከመጥፎ በመራቅ ባሮቹ ወደርሱ የሚመለሱበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡

3

ቀኑን የጾመና ሌሊቱን በመስገድ ቆሞ ያሳለፈ ሰው ያለፉት ወንጀሎቹ ይማሩለታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በእምነትና አላህ ዘንድ ያለውን ምንዳ በማሰብ የረመዳንን ወር የጾመ፣ ቀደም ሲል የሠራው ወንጀል ይማርለታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1910 /ሙስሊም 760) ‹‹በእምነትና አላህ ዘንድ ያለውን ምንዳ በማሰብ በረመዳን ወር (ተራዊሕና ተሃጁድን በመስገድ) የቆመ ሰው ቀደም ሲል የሰራው ወንጀል ይማርለታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1905/ ሙስሊም 759)

4

በረመዳን ውስጥ የዓመቱ ትልቅ ሌሊት ይገኛል፡፡

ይህች ሌሊት አላህ (ሱ.ወ) በመጽሐፉ፣ በዚች በርሷ ውስጥ የሚሠራ መልካም ሥራ፣ ለረዥም ዓመታት ከሚሠራ መልካም ሥራ እንደሚሻልና እንደሚበልጥ የተናገረላት ነች፡፡ አላህ (ሱ.ወ):- ‹‹መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺህ ወር በላጭ ናት፡፡›› ብሏል (አል ቀድር 3) እናም ይህችን ሌሊት በእምነትና አላህ ዘንድ ያለውን ምንዳ በማሰብ በመስገድ ቆሞ ያሳለፈ ሰው ቀደም ሲል የሰራው ወንጀል ይማርለታል፡፡ እርሷ በረመዳን ወር በመጨረሻዎቹ አስርት ሌሊቶች ውስጥ የምትገኝ ነች፡፡ ይህችን ሌሊት፣ ማንም ሰው በእርግጠኝነት በዚህ ዕለት ትሆናለች ብሎ መወሰንና መናገር አይችልም፡፡

የረመዳን ወር በኢስላማዊው ቀመር ዘጠነኛው ወር ነው፡፡