አምስቱ የግዴታ ሠላቶችና ወቅቶቻቸው

አምስቱ የግዴታ ሠላቶችና ወቅቶቻቸው


አላህ (ሱ.ወ) በሙስሊሞች ላይ በቀንና በሌሊት ውስጥ አምስት ሠላቶችን ግዴታ አደርጓል፡፡ እነኚህ ሠላቶች የሃይማኖት ምሶሶዎች ናቸው፡፡ ግዴታነታቸውም እጅግ አጽንዖት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ለነርሱም የሚከተሉትን ወቅቶች አድርጎላቸዋል፡፡

የፈጅር ሠላት፡ ሁለት ረካዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ጎሕ ከሚወጣበት ጊዜ ሲሆን፣ በአድማስ ላይ ብርሃን ሲፈነጥቅ ወይም ጨለማ መገፈፍ ሲጀምር ይከሰታል፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ፀሐይ ስትወጣ ነው፡፡


የዙህር ሰላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ፀሐይ ከመሐል አናት በምታዘነብልበት ጊዜ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ የእያንዳንዱ ነገር ጥላ ከራሱ ቁመት ጋር ሲስተካከል ነው፡፡


የዐሥር ሠላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው የዙህር ወቅት ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ይኸውም የእያንዳንዱ ነገር ጥላ ከራሱ ቁመት ጋር ሲስተካከል ነው፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ፀሐይ ስትጠልቅ ነው፡፡ አንድ ሙሰሊም ይህችን ሠላት፣ የፀሐይ ብርሃን ጮራ መድከምና መገርጣት ሳይጀምር ፈጠን ብሎ ሊሰግድ ይገባዋል፡፡


የመግሪብ ሠላት፡ ሦስት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ፀሐይ ከጠለቀችበትና ፍንጣቂዋ ከአድማስ ላይ ሲወገድ ወይም ሲደበቅ ነው፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ከፀሐይ መጥለቅ በኋላ የሚታየው ቀዩ ወጋገን ሲጠፋ ነው፡፡


የዒሻእ ሠላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ቀዩ ብርሃን ከጠፋበት ቅጽበት ነው፡፡ የሚያበቃው እኩለ ሌሊት ላይ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገጥምበት ጊዜ ጎህ እስኪ ቀድ ባሉት ሰዓቶችም ውስጥ ሊሰገድ ይችላል፡፡


አንድ ሙስሊም የሰላትን ወቅቶች በተመለከተ በወቅቶች ሰሌዳ መጠቀም ይችላል ነገር ግን ወደ ሰላት ለመግባት እሱን የመመልከት ግዴታ የለበትም