ሠላት ከአካላዊ አምልኮዎች ታላቋና ደረጇም የላቅ ነው፡፡ ቀልብን፣ አዕምሮንና ምላስን በአንድነት የሚያሳትፍ አምልኮ ነው፡፡ የሠላት አንገብጋቢነትን ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ይቻላል፡፡
ሠላት ከፍ ያሉ ደረጃዎች አሉት
1
ከኢስላም ማዕዘናት መካከል ሁለተኛው ማዕዘን ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «ኢስላም በአምስት መሰረታዊ ማዕዘናት ላይ ተገነባ፡፡ -ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ የለም፣ ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር፣ ሠላትን ማቋቋም፣….» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 8 /ሙስሊም 16) የአንድ ግንባታ ማዕዘን ወይም ምሰሶ፣ ያለርሱ ግንባታው የማይቆምበት መሰረቱ ማለት ነው፡፡
2
ሸሪዓዊ መረጃዎች፣ በሙስሊሞችና በካሃዲያን መካከል መለያ ነጥብ ያደረጉት ሠላትን ማቋቋምን ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «በአንድ ሰውና በክህደት መሐከል ያለው ነገር ሠላትን መተው ነው፡፡» ብለዋል፡፡(ሙስሊም 82) «በእኛና በእነርሱ መሐከል ያለው ኪዳን ሠላት ነው፡፡ እርሷን የተወ በርግጥ ክዷል፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 2621/ አል ነሳኢ 463)
3
አላህ (ሱ.ወ) ሠላትን በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ እንዲተገበር አዟል፡፡ በመንገደኛነት፣ በነዋሪነት፣ በሰላም፣ በጦርነት፣ በጤንነት፣ በህመምም ላይ ሆኖም በሚቻለው መጠን ሁሉ ይተገበራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «በሰላቶች ተጠባበቁ» ይላል፡፡ (አልበቀራ 238) ምዕመናን ባሮቹን ደግሞ፡- «እነዚያም እነሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የኾኑት፡፡»በማለት ይገልጻቸዋል፡ (አል ሙእሚኑን 9)
የሠላት ትሩፋት
የሠላትን ትሩፋት በማስመልከት በርካታ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች ተላልፈዋል፡፡ ከነሱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
1
ሠላት ወንጀሎችን ታብሳለች፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «አምስት ሠላቶችና ከጁምዓ እስከ ጁምዓ ትላልቅ ወንጀሎች እስካልተጣሱ ድረስ በመካከላቸው የሚፈፀሙትን ወንጀሎች ያብሳሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 233/ አል ቲርሚዚ 214)
2
ሠላት፣ለአንድ ሙስሊም በመላው ሕይወቱ የምታበራለት ብርሃኑ ናት፡፡ በመልካም ነገር ላይ ታግዘዋለች፡፡ ከመጥፎ ነገሮች ታርቃዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «ሠላት ብርሃን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 223)
3
ሠላት፣ የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምባት ጉዳይ ናት፡፡ እርሷ ካማረችና ተቀባይነት ካገኘች፣ የተቀረው ስራ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ እርሷ ተመላሽ ከሆነች የተቀሩት ስራዎችም ተመላሽ ይሆናሉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምበት ነገር ሠላት ነው፡፡ እርሷ ካማረች የተቀሩት ስራዎቹ ያምራሉ፡፡ እርሷ ከተበላሸች የተቀሩት ስራዎችም ይበላሻሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ሙዕጀሙል አውሰጥ ሊጠበራኒ 1859)

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ፣ በጦርነትና በአደጋ ጊዜ እንኳን ቢሆን፣ ብቻ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ ሠላትን እንዲተገብር አዟል፡፡
ሠላት ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?
ሠላት፣ በወር አበባና በወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች ሲቀሩ በማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ባለው፣ ሃላፊነትን ለመሸከም በደረሰ ሙስሊም ሁሉ ላይ ግዴታ ነው፡፡ ሴቶች በወር አበባ ወይም በወሊድ ደም ላይ ሆነው አይሰግዱም፡፡ ከጸዱና ደሙ ከተቋረጠ በኋላም ሠላትን አይከፍሉም፡፡ (ገጽ 96 ተመልከት)
ለአቅመ አዳምና ሄዋን መድረስ የሚወሰነው ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ ሲሟላ ነው፡፡
አስራ አምስት ዓመት መድረስ |
በፊት ለፊት ወይም በኋላ ብልቶች ዙሪያ ከርደድ ያለ ጸጉር ማብቀል |
በሕልም ወይም በንቃተ ሕሊና የፍቶት ፈሳሸን ማፍሰስ |
ለሴት፣ የወር አበባ መታየት ወይም ማርገዝ |