የሠላት መሰረታዊ ትርጉሙ፡ መማፀን ወይም መለመን ሲሆን፣ ባሪያን ከፈጣሪው ጋር የምታገናኝ መስመር ነች፡፡ በውስጧ ወሳኝ የሆኑ የባርነት መገለጫዎችን አቅፋለች፡፡ ወደ አላህ መሸሽና በርሱ መታገዝን አዝላለች፡፡ በሠላት ውስጥ ባሪያው ጌታውን ይለምናል፣ በሚስጥር ያወራል፣ ያወሳዋል፣ ነፍሱ ትጸዳለች፣ ባሪያው እውነተኛ ማንነቱን ያስታውስበታል፣በውስጧ እየኖረባት ያለችውን የዱንያን ትክክለኛ ገጽታ ይገነዘባል፡፡ የዚህች ዓይነቷ ሠላት፣ ባሪያው በአላህ ህግጋትና ድንጋጌ ላይ ጽናት እንዲኖረው፣ ከግፍ፣ ከዝሙትና ከአመፀኝነት እንዲርቅ ታደርገዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሠላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፤ ሠላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45)
