ስድስቱ የእምነት መሠረቶች

ስድስቱ የእምነት መሠረቶች

በኃያሉ አላህ የማመን


በኃያሉ አላህ የማመን ትርጉም፡-

የኃያሉ አላህ መኖርን እውነት ብሎ አምኖ መቀበል ነው፡፡ ጌትነቱን፣ አምላክነቱን፣ ማረጋገጥ ነው፡፡ በስሞቹንና በባህሪያቱ ማመን ነው።

ስለ እነዚህ አራት ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው ዘርዘር ባለ መልኩ እንነጋገራለን፡-




 

የአላህ ፍጥረት፡-


በአላህ መኖር ማመን ሰው በተፈጥሮው የሚያረጋግጠውና ሌላ ተጨማሪ መረጃ የማያስፈልገው ነገር ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ምንም የተለያየ ሃይማኖትና መንገድ ቢከተሉም በጣም በርካታ ሰዎች አላህ ለመኖሩ ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡

የእርሱን መኖር የሚያረጋግጥ ጥልቅ የሆነ ስሜት በቀልባችን ይሰማናል፡፡ በተፈጥሮው አማኝ በሆነው ስሜታችን ገፋፊነት መጥፎና አስቸጋሪ ነገር ሲገጥመን ወደርሱ እንሸሻለን፡፡ አንዳንዶች ለመሸፋፈንና ለመዘናጋት ሙከራ ቢያደርጉም፥ አላህ በእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ውስጥ ወደ ሃይማኖተኛነት የመዘንበል ስሜትን ፈጥሯል፡፡

እኛም አላህ ለተጣሪዎች ምላሸን ሲሰጥ፣ ለጠያቂዎች የጠየቁትን ሲቸር፣ ለተለማማኞች ፍላጎታቸውን ሲያሟላ ስለምናይና ስለምንሰማ፥ ይህ ሁኔታ አላህ ለመኖሩ እርግጠኛ መረጃ ይሆነናል፡፡


አላህ መኖሩ እጅግ ግልፅ የሆነ ነገር ነው፡ መረጃዎችን መዘርዘርም አያስፈልግም፡፡ ግልፅ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥም፡-


  • በሁሉም ሰው ዘንድ እንደሚታወቀው ማንኛውም ድርጊት አድራጊ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ በየጊዜው የምንመለከተው ይህ እጅግ በርካታ ፍጥረት አስገኚና ፈጣሪ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ እርሱም ኃያሉና ታላቁ አላህ ነው፡፡ አንድ ፍጡር ያለምንም ፈጣሪ ተገኘ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ራሱን በራሱ ፈጥሯል ማለትም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ራሱን በራሱ ሊፈጥር አይችልም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ወይስ ያለ አንዳች ፈጣሪ ተፈጠሩን ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?” (አልጡር፡35)
    በዚህ አንቀፅ መተላለፍ የተፈለገው መልእክት “እነርሱ ያለፈጣሪ አልተፈጠሩም፡፡ እነርሱም ራሳቸውን አልፈጠሩም፡፡ ስለዚህ ፈጣሪያቸው ሊሆን የሚችለው የተቀደሰውና ከፍ ያለው አላህ ነው” የሚል ነው፡፡

  • ሰማዩ፣ ምድሩ፣ ከዋክብቱ፣ ዛፎቹና ይህ ፍጥረተዓለም በአጠቃላይ የተመሠረተበት ሥርዓት ግልፅ በሆነ ሁኔታ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፥ የዚህ ፍጥረተዓለም ፈጣሪ አንድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እርሱም ከፍ ያለውና ከጉድለት የጠራው አላህ ነው፡፡ “… የዚያን ነገሩን ሁሉ ያጠነከረውና የአላህን ጥበብ (ተመልከት)፡፡” (አል-ነምል፡88)
    ክዋክብቶችን በምሳሌነት እንውሰድ፥ ፅኑ በሆነ አኳኋንና ስርዓት ነው የሚጓዙት፡፡ ሁሉም ኮከብ ያለምንም መሰናክልና መወላገድ በራሱ በሆነ ምህዋር ብቻ ይጓዛል፡፡ 
    አላህ እንዲህ ይላል “ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም፤ ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም፤ ሁሉም በመዞሪያቸው ውሰጥ ይዋኛሉ፡፡” (ያሲን፡40)

አትክሮት ላለውና ላስተነተነ ሰው አላህ ለመኖሩ ማስረጃ ከሚሆኑት ታላላቅ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሰው እራሱ ነው፡፡ አላህ የአዕምሮን፣ የስሜት ህዋሳትንና፣ ሙሉ የሆነና ስርዓት ያለው አፈጣጠርን በፀጋነት አጎናፅፎታል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “በነፍሶቻችሁም ውስጥ (ምልክቶች አልሉ)፤ ታዲያ አትመለከቱምን?” (አል-ዛሪያት፡21)



 

በኃያሉ አላህ ጌትነት የማመን ትርጉም፡-


ኃያሉ አላህ የሁሉም ነገር ባለቤት፣ ፈጣሪና ሲሳይን ሰጪ ነው ብሎ አምኖ መቀበልና እውነት ነው ብሎ በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በጌትነቱ ማመን ማለት ህይወት የሚሰጠውና የሚነሳው፣ የሚጠቅመውና የሚጎዳው እርሱ ብቻ ነው ብሎ ማመን ነው፡፡ የሁሉም ትዕዛዝ ባለቤት እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ መልካም ነገር ሁሉ በእጁ ነው፡፡ እርሱ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ነገሮችም ተጋሪ የለውም ብሎ ማመን ነው፡፡



ይህ እንግዲህ አላህ በተግባሩ ብቸኛ ነው ብሎ ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ እንደሚከተለው ማመን ያስፈልጋል፡- 


በፍጥረተ-ዓለሙ ውስጥ ያሉትን ነገሮች የፈጠረው አላህ ብቻውን ነው ከርሱ ሌላ ፈጣሪ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡” (አልዙመር፡62)

የሰው ተግባር ግን አንድን ነገር ወደ ሌላ ቅርፅ መቀየር ወይም እርስ በእርሱ ማቆራኘትና የመሳሰሉት እንጂ ከባድና ከምንም ተነስቶ የሚፈጥረው ነገር የለም፡ ፡ ሙት የሆነውን ነገር ወደ ህይወት ማምጣትም አይችልም፡፡


ለፍጥረታት ሁሉ ሲሳይን የሚሰጠው አላህ ነው፡ ፡ ከርሱ ውጪ ሲሳይን ሰጪ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “በምድር ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለችም ምግቧ በአላህ ላይ ቢሆን እንጂ…” (ሁድ፡6)


አላህ የሁሉም ነገር ባለቤት ነው፡፡ ከርሱ ሌላ የነገሮች እውነተኛ ባለቤት የለም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “የሰማያትና የምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፤ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡» (አል-ማኢዳህ፡12ዐ)


የሁሉም ነገር አስተናባሪ እርሱ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ ነገሮችን የሚየሰተናብር የለም፡፡ እንዲህ ይላል… «ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡» (አል-ሰጅዳህ፡5)

ሰሰው ህይወቱንና ጉዳዮቹን የሚያስተናብረው በተገደበና በተወሰነ መልኩ ነው፡፡ ባለውና በሚችለው ነገር ብቻ ነው የሚያስተናብረው፡ ፡ ይህ ማስተናበር ደግሞ ውጤታማ ሊሆንም ላይሆን ይችላል፡፡ ከጉድለት የጠራውና የኃያሉ ፈጣሪ ማሰተናበር ግን አጠቃላይ ነው፡፡ ከርሱ ቁጥጥር የሚወጣ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ያለማንምና ያለምንም ተቃውሞ ያሻውን ፈፃሚ ነው፡፡ እንዲህ ይላል “ንቁ፤ መፍጠርና ማዘዝ የርሱ ብቻ ነው፤ የዓለማት ጌታ አላህ (ክብሩ) )ላቀ፡፡» (አል-አዕራፍ፡54



“በምድር ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለችም ምግቧ በአላህ ላይ ያለ ቢሆን እንጂ፤” (ሁድ፡6)


በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘመን የነበሩ አረብ አጋሪዎች በአላህ ጌትነት ያምኑ ነበር፡-


በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘመን የነበሩ ከሃዲያን አላህ፥ ፈጣሪ፣ ንጉሥና አስተናባሪ መሆኑን ያምኑ ነበር፡፡ ይህ እምነታቸው ግን ወደ እስልምና እንዲገቡ አላደረጋቸውም… “ሰማያትንና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ፡፡” (ሉቅማን፡25)

አላህ የአለማት ጌታ መሆኑን፣ ፈጣሪ፣ ባለቤትና አስተናባሪ መሆኑን ያረጋገጠ ሰው፣ አላህን በብቸኝነት ሊያመልክ ይገባዋል፡፡ የአምልኮ ተግባራትን ያለማንም ተጋሪ ለርሱ ብቻ ማዋል ይኖርበታል፡፡

አንድ ሰው የፍጥረተ-ዓለሙ ፈጣሪ፣ አስተናባሪ፣ ህይወት ሰጪና ነሺ አላህ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የአምልኮ ዓይነቶችን ከርሱ ውጪ ላሉ ነገሮች ማዋል በጣም የማያስገርም ነገር ነው፡፡ ይህ አስጠያፊ በደልና ታላቅ ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሉቅማን ልጃቸውን ሲመክሩ እንዲህ ያሉት “… ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ፤ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና ያለውን (አስታውስ)፡፡” (ሉቅማን፡13)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) አላህ ዘንድ ታላቅ ወንጀል ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “አላህ ፈጥሮህ ሳለ ለርሱ ተጋሪን ማድረግህ ነው፡፡” በማለት መልሰዋል፡፡ (አልቡኻሪ፡4207 ሙስሊም፡86)




በአላህ ጌትነት ማመን ቀልብን ያረጋጋል፡-


አንድ የአላህ ባሪያ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ከሆነ፥ ከኃያሉ አላህ ውሳኔ ውጭ ሊሆን የሚችል ፍጡር እንደሌለ ይገነዘባል፡፡ ምክንያቱም የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት አላህ ሲሆን ከጥበቡ ጋር በሚስማማ መልኩ እንዳሻው የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡

አንድ የአላህ ባሪያ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ከሆነ፥ ከኃያሉ አላህ ውሳኔ ውጭ ሊሆን የሚችል ፍጡር እንደሌለ ይገነዘባል፡፡ ምክንያቱም የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት አላህ ሲሆን ከጥበቡ ጋር በሚስማማ መልኩ እንዳሻው የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡

ይህ እምነት ያለው ሰው ቀልቡ በአላህ ላይ ብቻ ይንጠለጠላል፡፡ እርሱን ብቻ ይጠይቃል፣ ከርሱ ብቻ ይፈልጋል፡፡ በሁሉም የህይወት ጉዳዩ የሚመካው በርሱ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ሁሉንም የህይወት ገጠመኝ በፅናት፣ በቁርጠኝነትና በተረጋጋ መንፈስ ይጋፈጣል፡፡ ምክንያቱም ለህይወቱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት ሁሉንም ሰበብ ከመምከሩ ጎን ለጎን የአላህን እርዳታም ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነቱንም ይወጣል፡፡

ይሄኔ ነፍሱ ትረጋጋለች፡፡ ሰው ዘንድ ያለውን አይከጅልም፡፡ ሁሉም ነገር ያለው በአላህ እጅ ነው፡፡ የሚፈልገውን ይፈጥራል፡፡ ይመርጣልም፡፡ 

በአላህ ጌትነት ማመን ቀልብን ያረጋጋል



 

በኃያሉ አላህ የማመን ትርጉም፡-


ግልፅም ሆነ ድብቅ የአምልኮ ዓይነቶች ሁሉ የሚገቡት ለኃያሉ አላህ ብቻ ነው ብሎ በቁርጠኝነት አምኖ መቀበል ማለት ነው፡ ሁሉንም የአምልኮ ዓይነቶች ለአላህ ብቻ እናውላለን፡፡ ዱዓእን፣ ፍራቻን፣ መመካትን፣ እርዳታ መፈለግን፣ ሶላትን፣ ዘካንና ፆምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአላደህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ “አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እርሱ እጅግ በጣም ርኀሩኀ አዛኝ ነው፡፡” (አል-በቀራህ፡163)

አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን አላህ ነግሮናል፡፡ ይህ ማለት የሚመለከው አንድ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ከአላህ ሌላ አምላክ ተደርጎ ሊይያዝ የሚገባው ነገር የለም፡፡ ከርሱ ውጭ ማንም አይመለክም፡፡


አላህን በአምልኮ አንድ ማድረግ «ከአላህ በስተቀር በእውነተ የሚመለክ አምላክ የለም» የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ነው፡፡


በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነት፡-


በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነትን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግልፅ እንዲሆን ማድረግ፡-

1

ሰውም ሆነ ጋኔን የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ የተፈጠሩት አላህን በብቸኝነትና ያለምንም ተጋሪ ለመግገዛት ነው፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል…«ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡» (አል-ዛሪያት፡56)

2

የአላህ መልእክተኞች የተላኩት መለኮታዊ መፅሐፍት የወረዱት ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ ዓላማቸው በእውነት መመለክ የሚገባው አላህ መሆኑን ለማፅናት ሲሆን ከርሱ ውጭ በሚመለኩ ነገሮች ደግሞ ለመካድ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልእክተኛን በእርግጥ ልከናል፤” (አል-ነሕል፡36)

3

በሰው ልጅ ላይ የመጀመሪያው ግዴታ አላህን በብቸኝነት መገዛት ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሙዓዝ ቢን ጀበልን ወደ የመን ለሰበካ በላኩት ጊዜ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነገር ነግረውት ነበር፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት… “የመፅሐፍቱ ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ክርስቲያኖች /አይሁዶች/ ያጋጥሙሃል በመጀመሪያ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለከ አምላክ የለም ወደ ሚለው ቃል ጥራቸው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡1389 ሙስሊም፡19)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ለማለት የፈለጉት “በሁሉም የአምልኮ ዓይነቶች አላህን ብቻ አምልኩ በላቸው፡፡” ለማለት ነው፡፡

4

“ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም፥ በአላሀ አምላክነት ማመን ነው፡፡ አምላክ ማለት የሚመለክ ማለት ነው፡፡ ከአላህ በቀር በዕውነት የሚመለክ የለም፡፡ ማንኛውም የአምልኮ ዓይነት ከርሱ ውጭ ለማንም አናውልም፡፡

5

በአላህ አምላክነት ማመን፣ አዕምሮ የሚመራው አሳማኝ የሆነ፣ አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ፣ ባለቤትና አዘጋጅ ነው ብሎ የማመን ውጤት ነው፡፡



 

ይህ ማለት፥ አላህ በመፅሐፉ ውስጥ ወይም መልእክተኛው በስሱናቸው ያፀደቁትንና አላህ እራሱን የሰየመበትን ስም እንዲሁም ማንነቱን የገለፀበትን ባህሪ ለአላህ በሚገባው መልኩ ማመን ማለት ነው፡፡

ከጉድለት የጠራ የሆነው አላህ ምርጥ የሆኑ ስሞችና ሙሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት፡፡ በስሙም ሆነ በባህሪያቱ ፍፁም አምሳያ የሌለው ጌታ ነው፡፡ እንዲህ ይለናል “የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱም ሰሚው ተመልካቱ ነው፡፡” (አል-ሹራ፥11)

አላህ በሁሉም ስሞቹና ባህሪያቱ ከየትኛውም ፍጡር ጋር ፍፁም የማይመሳሰልና የጠራ ነው፡፡


ከአላህ ስሞች ውስጥ የተወሰኑት፡-


አላህ እንዲህ ይላል “እጅግ በጣም ርኀሩኀ በጣም አዛኝ” (አል-ፋቲሐህ፡3)

አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡” (አል ሹራ፡11)(አል ሹራ 11)

አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡” (ሉቅማን፡9)

አላህ እንዲህ ይላል “አላህ ከርሱ በቀር ሌላ አምላከ የለም፤ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፤” (አል-በቀራህ፡ 255)

አላህ እንዲህ ይላል “ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለሆነው፡፡” (አል-ፋቲሐህ፡2)




በአላህ ስሞችና ባህሪያት የማመን ፍሬዎች፡-


1

ኃያሉ አላህን ያሳውቀናል፡- በአላህ ስሞችና ባህሪያት ያመነ ሰው ስለ አላህ ያለው እውቀት ይጨምራል፡፡ በአላህ ላይ ያለው እርግጠኛ እምነትም ይጨምራል፡፡ ስለ አላህ አንድነት ያለው ዕምነት ይጠነክራል፡፡ የአላህን ስሞችና ባህሪያት ያወቀ ሰው፥ ቀልቡ በአላህ ታላቅነት፣ ውዴታና አክብሮት መሞላቱ የግድ ነው፡፡

2

አላህን በስሞቹ ማወደስ እንችላለን፡፡ ይህ ምርጥ ከሆኑ የዚክር (የውዳሴ) ዓይነቶች ውስጥ ይካተታል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብዙ ማውሳትን አውሱት፡፡” (አል-አሕዛብ፡ 41)

3

ስምና ባህሪውን ካወቅን፥ በስሞቹና በባህሪያቱ ልንማፀነው አንችላለን፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ለአላህም መልካም ስሞች አሉት ስትፀልዩም በርሷም ጥሩት” (አል-አዕራፍ፡ 180)በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፡- አንተ ሲሳይን ሰጪ ሆይ! ሲሳይን ስጠኝ፡፡ አንተ ይቅር ባይ ሆይ! ይቅር በለኝ፡፡ አንተ አዛኝ ሆይ! እዘንልኝ… ማለት እንችላለን፡፡





> በአላህ ስሞችና ባህሪያት ማመን፡-


አምልኮ (ኢባዳ) ማለት፡- አላህ የሚወደውና የሚደሰትበት እንዲሁም ንግግሮችንና ተግባራትን ሁሉ የሚያጠቃልል ስም ሲሆን ሰዎች ይተገብሩት ዘንድ አላህ ያዘዘው ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር እንደ ሶላት፣ ዘካ፣ ሐጅ ግልፅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አላህንና መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) እንደ መውደድ፣ አላህን እንደ መፍራት፣ በርሱ እንደመመካትና ከርሱ እርዳታን እንደመፈለግ ስውር ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎችም አንደዚሁ፡፡



በሁሉም የሀይወት ዘርፍ አላህን ስለማምለክ፡-



ወደ አላህ መቃረብን ዓላማው ያደረገ የማንኛውም አማኝ ሙእሚን ተግባር በአምልኮ ዒባዳ ውሰጥ ይካተታል፡፡

በእስልምና ሃይማኖት መሠረት አምልኮ በሶላት፣ በፆምና በመሳሰሉ የፀሎት ስነ-ሥርዓቶች የተገደበ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ዓይነት ጠቃሚ ተግባር መልካም የሆነን ዓላማ (ኒያ) እስካነገበ ድረስ፥ የአምልኮ ተግባር እንደሆነ የሚቆጠር ሲሆን ተግባሪውም አላህ ዘንድ ይመነዳበታል፡፡

የአላሀ ትዕዛዝ በአግባቡ ለመፈፀም ይቻል ዘንድ አካላዊ ጥንካሬ ለማግኘት በሚል ዓላማ አንድ ሙስሊም ቢመገብ፣ ቢጠጣና ቢተኛ አላህ ዘንድ ምንዳ ያገኝበታል፡፡

ስለዚህ ሙስሊም ህይወቱን በሙሉ ለአላህ እያስገዛ ነው ማለት ነው፡፡ አላህን ለመታዘዝ ሰውነቱ ይጠነክር ዘንድ ይመገባል፡፡ በዚህ ዓላማ በመመገቡ አላህን እያመለከ ነው፡፡ ከአመንዝራነት ራሱን ለመጠበቅ በሚል ዓላማ ትዳር ይመሰርታል፡፡ ጋብቻው በራሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንለታል፡፡ ልክ እንደዚሁ ዓላማው ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ንግዱ፣ ሥራው፣ ቢዝነሱ ሁሉ አምልኮ ይሆንለታል፡፡ እውቀት መፈለጉ፣ መመራመሩ፣ መፈላሰፉ፣ መፍጠሩ ሁሉ እንደ አምልኮ ይቆጠርለታል፡፡

አንዲት እንስት ባልዋን፣ ልጆቿንና ቤቷን መንከባከቧ በርሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንላታል፡፡

በሁሉም የህይወት ዘርፍ የሚከናወኑ ጠቃሚ ተግባራት በሙሉ መልካም ዓላማና ዕቅድን መነሻ አድርገው እስከተፈፀሙ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ይቆጠራሉ፡፡

> የአላህን ምንዳ መከጀል ዓላማ ያደረገ (ኒያ ያለው) ማንኛውም ተግባር እንደ አምልኮ (ዒባዳ) የሚቆጠር ሲሆን፥ በዚህ ተግባርም ምንዳ (አጅር) ይገኝበታል፡፡



አምልኮ (ዒባዳ) ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡-



አላህ እንዲህ ይላል… “ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡ አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው፡፡” (አል- ዛሪያት፡56-58)

አላህ ሰውንም ሆነ ጋኔን የፈጠረበት ጥበብ እርሱን ይግገዙ ዘንድ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ፍጥረታት አላህን የሚግገዙት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ አላህ ከእነርሱ ጥቅም ፈላጊ ሆኖ አይደለም፡፡

ሰው የተፈጠረበትን መለኮታዊ ይህን ዓላማ ዘንግቶ በዓለማዊ ህይወት ውስጥ ሰጥሞ ከቀረ፥ በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ፍጥረታት የሚለየው ምንም ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንስሳቶች ከሰው በተቃራኒ በቀጣዩ ዓለም ስለሰሩት ሥራ አይጠየቁም እንጂ እነርሱም ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይፈነጥዛሉ፡፡

አላህ እንዲህብሏል… “… እነዚያም የካዱት (በቅርቢቱ ዓለም) ይጠቀማሉ፤ እንስሳዎችም እንደሚበሉ ይበላሉ እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት፡፡” (ሙሐመድ፡12)

ተግባርና ዓላማቸው ከእንስሳ ጋር ተመሳስሏል፡፡ ነገርግን ከእንስሳ የሚለያቸው በመጨረሻው ቀን የስራቸውን ውጤት ማግኘታቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ምንም ከማያውቁት እንስሳት በተለየ አዕምሮ ያላቸው፣ የሚገነዘቡና የሚያውቁ በመሆናቸው ነው፡፡



የአምልኮ (ዒባዳ) መሠረቶት



አላህ እንተገብረው ዘንድ ያዘዘን አምልኮ በሁለት ዋና ዋና መሠረቶች ላይ የተገነባ ነው፡-

አንደኛ፡- ሙሉ የሆነ ፍራቻና መተናነስ፡-

ሁለተኛ፡- ሙሉ የሆነ ውዴታን ለአላህ ማዋል፡-

አላህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ያደረገው አምልኮ፥ ለአላህ ብቻ የሚውል ሙሉ የሆነ ፍራቻ፣ መተናነስና ዝቅ ማለትን በውስጡ ያካተተ ከመሆኑ ጎን ለጎን ሙሉ የሆነ ውዴታና ክጃሎትን ለአላህ ብቻ ማዋልን ይጠይቃል፡፡

ስለሆነም ልክ ምግብን ወይም ገንዘብን እንደምንወደው ሁሉ አላህንም ፍራቻና መተናነስን ባላካተተ አኳኋን የምንወደው ከሆነ አምልኮ አይባልም፡፡ ልክ እንደዚሁ አውሬና ጨቋኝ መንግስትን እንደምንፈራው ሁሉ አላህንም ውዴታን ባላጎዳኘ አኳኋን የምንፈራው ከሆነ ከአምልኮ አይቆጠርም፡፡ ሆኖም ግን በስራችን ውስጥ ውዴታንና ፍራቻን ካቆራኘን ትክክለኛ አምልኮን አስገኝተናል፡፡ አምልኮ ደግሞ ሊውል የሚገባው ለአላህ ብቻ ነው፡፡




የአምልኮ ቅድመ ሁኔታዎች፡-



  • አምልኮ የተስተካከለና አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡
    • 1

      የመጀመሪያው አምልኮን ያለ ምንም ተጋሪ ለአላሀ ብቻ ማዋል ሲሆን

    • 2

      ሌላው ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከአከናወኑት የአምልኮ ተግባር ጋር የሚጣጣምና የሚስማማ መሆን ይኖርበታል፡፡

አላህ እንዲህ ብሏል “አይደለም እርሱ በጎ ሰሪ ሆኖ ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው ለርሱ በጌታው ዘንድ ምንዳው አለው፤ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነሱም አያዝኑም፡፡” (አል-በቀራህ፡112)
በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው” ማለት፥ የአላህን አንድነት በተግባር ያረጋገጠና አምልኮን ለርሱ ብቻ ያጠራ ማለት ነው፡፡
“በጎ ሰሪ ሆኖ” የሚለው ደግሞ፥ የአላህን ህግና የመልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) አርዓያነት የሚከተል ማለት ነው፡፡



ሥራን ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና (መንገድ) ጋር ማጣጣም ማለት እንደ ሶላት፣ ፆምና አላህን ማውሳት የመሳሰሉት ተግባራትን እርሳቸው ባከናወኑት መሠረት መፈፀም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ሌሎች የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለጥሩ ዓላማ (ኒያ) እስካከናወናቸው ድረስ ከአምልኮ ተግባራት ተርታ የሚመደቡ ቢሆንም፥ ከአላህ መልእክተኛ ሱንና ጋር የግድ እንዲጣጣሙ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ባይሆን መጠንቀቅ የሚኖርብን ሸሪዓውን የሚቃረን ሐራም ነገር ላይ ላለመውደቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የአላህን ትዕዛዝ ለመተግበር ጠንካራ ያደርገው ዘንድ ስፖርት ቢሰራ ወይም የቤተሰቡንና የልጆቹን ወጪ ለመሸፈን ስራ ቢሰራ ኒያውን እስካሳመረ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ቢቆጠርለትም ከሱንና ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡


> ሺርክ (የአምልኮ ተግባርን ከአላህ ዉጪ) ላለ አካል ማጋራት


  • ሺርክ በአላህ አምላክነት ላይ ያለንን እምነት የሚፃረር ነገር ነው፡፡ በአላህ አምላክነት ማመንና የአምልኮ ተግባራትን ለርሱ ብቻ ማዋል ከታላላቅና ወሳኝ ከሆኑ ግዴተዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ መሆኑ እርግጥ ከሆነ፥ ከዚህ በተመሳሳይ መልኩ ለአላህ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ተግባር ለሌላ አካል ማጋራት ደግሞ አላህ ዘንድ የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ንሰሃ ካልገቡ በቀር አላህ በፍፁም የማይምረው ብቸኛ ወንጀል ነው፡፡ 

    አላህ እንዲህ ይላል… “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኃጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡” (አል-ኒሳእ፡48) 

    ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) አላህ ዘንድ ከወንጀሎች ሁሉ ታላቁ ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “አላህ ፈጥሮህ ሳለ ለርሱ ተጋሪ ማድረግህ ነው” በማለት መልሰዋል፡፡ (አል-ቡኻሪ፡ 4207 / ሙስሊም፡ 86)

  • በአላህ ማጋራት ስራን በሙሉ ከንቱና ውድቅ ያደርጋል፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል፡፡ … “…ባጋሩም ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነርሱ በታበሰ ነበር፡፡” (አል-አንዓም፡88) 

    በአላህ አጋርቶ ንሰሃ ሳይገባ የሞተ ሰው ዕጣፈንታው ዘላለም በጀሃነም እሳት መቀጣት ይሆናል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ …”እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (አል-ማኢዳህ፡72)



ሺርክ ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ታላቅና ታናሽ


  1. ታላቁ ሺርክ፡- ይህ ማለት አንድን የአምልኮ (ዒባዳ) ዓይነት ከአላህ ውጪ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ አንድ አላህ የሚወደውን ንግግርም ሆነ ተግባር ለአላህ ብቻ ካዋልነው አንድነቱን አፀደቅን ወይም አመንበት ማለት ነው፡፡ ይህን ተግባር ከርሱ ሌላ ለሆነ አካል ካዋልነው ደግሞ፥ ክደነዋል አጋርተንበታል፡፡

    ለእንዲህ ዓይነቱ የሺርክ ተግባር ምሳሌን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ከአላህ ውጪ ያለን አካል ከህመም እንዲያሽረን፣ ሲሳይን እንዲያሰፋልን ከጠየቅነውና ከለመንነው በታላቁ የሺርክ ተግባር ላይ ወድቀናል ማለት ነው፡፡ ከአላህ ውጪ ለሆነ ነገር ብንሰግድ ወይም በርሱ ላይ ብንመካም እንደዚያው ነው፡፡

    አላህ እንዲህ ይላል … “ጌታችሁም አለ፡- ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሃነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡” (አል-ሙእሚን፡60)

    እንዲህም ይላል … “… ምእምናንም እንደ ሆናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ አሉ፡፡” (አል-ማኢዳህ፡23)

    ሌላ ሱራ ላይም እንዲህ ብሏል…”ለአላህም ስገዱ ተገዙትም፡፡” (አል ነጅም፡ 62)

    እነዚህን ተግባራት ከአላህ ሌላ ላለ አካል ያዋለ ሰው አጋሪ እንዲሁም ከሃዲ ይሆናል፡፡

  2. ትንሹ ሺርክ፡- ይህ ደግሞ ወደ ታላቁ ሺርክ ሊያደርስ የሚችል ንግግር ወይም ተግባር ነው፡፡ ትንሹ ሺርክ ታላቁ ሺርክ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡

    ለዚህኛው የሚሆን ምሳሌ መጥቀስም ይቻላል፡- ሰው አንዲያይለት በማሰብ ሶላትን ማስረዘም ወይም ሰዎች እንዲያደንቁት በማሰብ ቁርኣን ሲያነብ ወይም አላህን ሲዘክር ድምፁን ማድረግና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) “እኔ ለእናንተ በጣም ከምፈራላችሁ ነገር ውስጥ አንዱ ትንሹ ሺርክ ነው፡፡” በማለት ሲናገሩ ሰሃቦችም “አንቱ የአላህ መልእክተኛ ትንሹ ሺርክ ምንድ ነው?” በማለት ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም “የይዩልኝ ስራ ነው፡፡” በማለት መልስ ሰጡ (አህመድ፡2363)

    ሆኖም ግን ፍፁም ለሰው ተብሎ የሚደረግ የአምልኮ ተግባር ሶላትም ሆነ ፆም የመናፍቅ ሥራ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ከእስልምና ሃይማኖት ውጪ የሚያደርግ ታላቅ የሺርክ ተግባር ነው፡፡



ከሰው መፈለግና ሰውን አንዳንድ ነገር መጠየቅ የሺርክ ተግባር ነውን?



የእስልምና ሃይማኖት የተደነገገው የሰውን አዕምሮ ከንቱ ከሆኑ እምነቶች ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ የተደነገገው የሰው ልጅ ከአላህ ውጪ ላለ አካል ዝቅ እንዳይል ነው፡፡

ለሙታንም ሆነ ግዑዝ ለሆኑ አካላት ዝቅ ብሎ በመተናነስ ፍላጎትን መጠየቅ ህገ-ወጥ የሆነ ተግባር ነው፡፡ ይህ ከንቱ እምነትና ሺርክ ነው፡፡

ነገር ግን አጠገባችን ያለንና ህይወት ያለውን ሰው አቅሙ የሚችለውን ነገር እንዲያደርግልን ብንጠይቀው ወንጀል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ውሃ ውስጥ የሰጠመ ሰው ህይወቱን ያተርፈው ዘንድ ሰውን መጠየቁ፣ ወይም አንድ ሰው ዱዓእ እንዲያደርግልን ብንጠይቅ እስልምና የሚፈቅደው ህጋዊ ተግባር ነው፡፡


  • ሙታንን ወይም ግዑዝ አካላትን መከጀልና መማፀን የሺርክ ተግባር ነውን?
    • አዎን

      ይህ ግልጽ አይደለም ኢማንን የሚቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም ሙታንና ግዑዛን ነገሮች፣ ጥያቄውን መስማትም ሆነ ምላሽ መስጠት አይችሉም፡፡ ልመና (ዱዓ) አምልኮ ነው። በመሆኑም ከአላህ ሌላ ለሆነ አካል አሳልፎ መስጠት ማጋራት ነው፡፡ ግልጽ አይደለም በታወጀበት ዘመን የነበሩ ዐረቦች ያጋሩ የነበሩት ግዑዛንንና ሙታንን በመለመን ነበር፡፡

    • አይቻልም(በፍፁም)

      ሕያው ሆኖ ጥያቄህንና ልመናህን ሊሰማ የሚችልን አካል መለመንህና መጠየቅህ፡፡ እርሱ በሚችለው ነገር ላይ እንዲረዳህና እንዲያግዝህ በጠየቅከው ዓይነት? ልመናህን ለመመለስና ጥያቄህን ለመስማት ይችላልን?

      • አዎን

        ይህ ተገቢ ልመና ነው፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡ በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነትና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከሚከሰቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡

      • አይቻልም(በፍፁም)

        ከሕያው ሰው እርሱ የማይችለውን ነገር ከርሱ መፈለግ ወይም መከጀል ማለት አንድ መውለድ የማይችል መካን፣ ከሕያው ሰው ፃድቅ ልጅ እንዲሰጠው እንደመለመን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከኢስላም ጋር የሚቃረን ትልቁ የማጋራት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ ሌላ ያለን አካል መለመን ነውና፡፡

 > በህይወት ያለና አጠገባችን የሆነን ሰው አቅሙ የሚፈቅደውን ነገር እንዲያደርግልን ብንጠይቀው፥ እንደ የዕለት ውሎ የሚቆጠር ህጋዊ የሆነ ተግባር ነው፡፡


ከፍ ያሉ የእምነት ደረጃዎች


ከፍ ያሉ የእምነት ደረጃዎች፡-


እምነት የተለየዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ የአንድ ሙስሊም እምነት መዘንጋቱንና ሐጢአቱን መነሻ አድርጎ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ለአላህ ባለው ታዛዥነት፣ አምልኮና ፍራቻ ልክ እምነቱ ይጨምራል፡፡

የእምነት ከፍተኛው ደረጃ ሸሪዓው እንዳለው «ኢህሣን» በሚል ይተወቃል፡፡ ስለ «ኢህሣን» ምንነት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል… “አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና፥ አላህን ስትገዛው እያየኸው እንደምትገዛው ሆነህ ተገዛው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡50 ሙስሊም፡8)

ቆመህም ሆነ ተቀምጠህ፣ በደስታም ሆነ በሃዘን ወቅት በአጠቃላይ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆነህ አላህን ማስታወስ ይኖርብሃል፡፡ አላህ ምንግዜም በቅርበት ይመለከትሃል፡፡ እየተመለከተህ መሆኑን ካወቅህ ወንጀል አትፈፅምም፡፡ እርሱ ካንተ ጋር መሆኑን የምታውቅ ከሆነ ፍርሃትም ሆነ ተስፋ መቁረጥ አይቆጣጠሩህም፡፡ በእርግጥ አላህን በሶላትህና በዱዓህ አያናገርከው ብቸኝነት ሊሰማህ አይችልም፡፡

የሰወርከውንም ግልፅ ያደረግከውንም አላህ እንደሚየውቅ እየተገነዘብክ ነፍስህ ወደ ኃጢአት ልትገፋፋህ አትችልም፡ ፡ኃጢአት ላይ ተዳልጠህና ተሳስተህ ከወደቅህ ደግሞ ወደ አላህ በመመለስ ምህረቱን ትማፀነዋለህ እርሱም ይምርሃል፡፡




አላህን የማመን ፍሬዎች


አላህን የማመን ፍሬዎች፡-


1

አላህ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ለምእመናን ይከላከልላቸዋል፡፡ ከጭንቅ ያድናቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላሀ እንዲህ ይላል “አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡” (አል-ሐጅ ፡ 38)

2

በአላህ ላይ የሚኖረን እምነት መልካም የሆነን ህይወት፣ ደስታንና ፍስሃን ያጎናፅፋል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል … “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤” (አል-ነሕል፡97)

3

እምነት ነፍስን ከከንቱ እምነቶች ፅዱ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው፥ ጉዳዩን ሁሉ ለአንድ አላህ ብቻ ይተዋል፡፡ እርሱ የዓለማት ጌታ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ እውነተኛ አምላክ የለም፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው ፍጡርን አይፈራም፡፡ ማንንም ሰው በቀልቡ አይከጅልም፡፡ ከዚህም በላይ ከንቱና አላስፈላጊ ከሆኑ እምነቶች ራሱን ነፃ ያደርጋል፡፡

4

የኢማን ከፍተኛ ተፅዕኖ፡- የአላህን ውዴታ ያስገኛል፡፡ ጀነት ያስገባል፡፡ ቋሚና ዘላለማዊ ለሆነ የፀጋ ስኬት ያበቃል፡፡ ሙሉ የአላህ እዝነትን ያስገኛል፡፡




በመላእክት ማመን



በመላእክት የማመን ትርጓሜ



ይህ የመላእክትን መኖር፣ እነርሱ ከሰው ዘርም ከአጋን”ትም ዓለም ያልሆኑ የስውር ዓለም ፍጡራን እንደሆኑ በቁርጠኝነት ማጽደቅ ነው፡፡ እነርሱ የተከበሩና አላህን ፈሪዎች ናቸው፡፡ አላህን ትክክለኛ የሆነ መገዛትን ይገዙታል፡፡ እርሱ ያዘዛቸውን በመፈፀም ያስተናብራሉ፡፡ በአላህ ላይ ፈፅሞ አያምጹም፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «(መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው፡ ፡ በንግግር አይቀድሙትም (ያላለውን አይሉም) እነሱም በትዕዛዙ ይሰራሉ፡፡» (አል አንቢያ 26-27)

በእነሱ ማመን ከኢማን ስድስት መሠረቶች አንዱ መረት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፡ ምዕመናኖችም (እንደዚሁ) ሁሉም በአላህ በመላእክቱም በመጻሕፍትቱም በመልክተኞቹም…. አመኑ፡፡» (አል በቀራ 285)

ኢማንን አስመልክተው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍት፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)



በመላእክት ማመን ምንን ያካትታል?



1

በመኖራቸው ማመን፡ እነርሱ የአላህ ፍጥረታት እንደሆኑ እናምናለን፡፡ በተጨባጭ ያሉ ናቸው፡፡ አላህ የፈጠራቸው ከብርሃን ነው፡፡ እርሱን በመገዛትና በመታዘዝ ላይ አግርቷቸዋል፡፡ 

2

ከነርሱ መካከል እንደ ጂብሪል (ዐ.ሰ) በስሙ ያወቅነውን እስከነስሙ እናምናለን፡፡ በስማቸው ያላወቅነውናቸውንም በጥቅሉ እናምንባቸዋለን፡፡ 

3

ከባህሪያቸው በምናውቀው ማመን፡፡ ከባህሪያቸው መካከል፡


• እነርሱ የስውር ዓለም ፍጥረታት መሆናቸው፡፡ ለአላህ የሚገዙ ፍጡራን ናቸው፡፡ ከቶም የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ባህሪ የላቸውም፡፡ እንደውም እነሱ አላህን ለመታዘዝ ሙሉ በሙሉ የተገሩ የአላህ ባሮች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ያዘዛቸውን በመጣስ አያምጡም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሰራሉ፡፡» (አል ተህሪም 6)


• የተፈጠሩት ከብርሃን ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «መላእክት ከብርሃን ተፈጠሩ፡፡» ሙስሊም 2996


• ክንፎች አሏቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለመላእክት ክንፍን እንዳደረገ ተናግሯል፡፡ የክንፎቻቸው ብዛት ይበላለጣል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሦስት ሦስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፤ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡» (ፋጢር 1)


4

በአላህ ትዕዛዝ መሰረት እነርሱ ከሚያከናውኗቸው ስራዎቻቸው ባወቅነው ማመን፡፡ ከነርሱ መካከል፡-


• መለኮታዊ ራዕይን ወደ መልክተኞች በማምጣት የተወከለ አለ፡፡ እሱም ጂብሪል (ዐ.ሰ) ነው፡፡


• ነፍስን በማውጣት የተወከለም አለ፡፡ እርሱም የሞት መልአክና ተባባሪዎቹ ናቸው፡፡


• መልካምም ሆነ እኩይ፣ የባሮችን ስራ መዝግቦ በማቆየት ወይም በመጠበቅ የተወከሉ አሉ፡፡ እነሱም የተከበሩ ፀሐፍት መላእክት ናቸው፡፡



በመላእክት የማመን ፍሬ ወይም ጥቅም፡፡


በመላእክት ማመን በሙእሚን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ከነኚህ ጥቅሞች መካከል የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡፡

1

የአላህን ልቅና፣ ኃይል፣ ሙሉዕነትና ችሎታ ያሳውቃል፡፡ የፍጥረታት ትልቅነት የፈጣሪያቸውን ትልቅነት ያሳያል፡፡ በመሆኑም አንድ ሙዕሚን በመላእክት በማመኑ ለአላህ የሚሰጠው ደረጃና ለርሱ ያለው ከበሬታ ይጨምራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ብዙ ክንፎች ያሏቸው መላዕክትን ከብርሃን የፈጠረ ነው፡፡ 

2

አላህን በመታዘዝ ላይ ጽናትን ያጎናጽፋል፡፡ መላዕክት ስራዎቹን በሙሉ እንደሚፅፉ የሚያምን ሰው፣ ይህ እምነቱ የአላህ ፍራቻ እንዲያድርበት ያደርጋል፡፡ በይፋም ሆነ በድብቅ በአላህ ላይ አያምጽም፡፡  

3

አንድ አማኝ በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ አላህን የሚታዘዙ መላእክት አብረውት በተሟላና ባማረ መልኩ እንዳሉ በእርግጠኝነት በሚረዳ ጊዜ አላህን የመታዘዝ ትዕግስትን ይላበሳል፡፡ መላመድንና መረጋጋትን ያገኛል፡፡ 

4

ከመላእክት መካከል የሚጠብቋቸውና የሚከላከሉላቸው በማድረግ አላህ ለአደም ልጆች በቸረው ትኩረቱና ክትትሉ ማመሰገን፡፡ 


ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰማይ በውስጧ ባሉት ፍጥረታት እንደተጨናነቀች ተናግረዋል፡፡ በውስጧ የስንዝር ያክል ቦታ እንኳን ቢሆን የቆመ ወይም ያጎነበሰ፣ ሩኩዕ ያደረገ ወይም በግንባሩ የተደፋ፣ ሱጁድ ያደረገ መልኣክ ቢኖር እንጂ ክፍት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡


በመጽሕፍት ማመን



በመጽሐፍት የማመን ትርጓሜ



አላህ (ሱ.ወ) በመልክተኞቹ ላይ ወደ ባሮቹ ያወረዳቸው መጽሐፍት እንዳለው፣ እነኚህ መጽሐፍት በሙሉ የአላህ ቃልና ንግግር እንደሆኑ ማመን ነው፡፡ ለክብርና ልቅናው ተገቢ በሆነ መልኩ በርግጥ ተናግሯል፡፡ እነኚህ መጽሐፍት በውስጣቸው ለሰው ልጅ፣ ለሁለቱም ዓለም የሚሆን መመሪያና ብርሃን የያዙ እውነቶች ናቸው ማለትን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ፡፡

በመጽሐፍት ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ማዕዘን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው፣ በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡» (አል ኒሳእ 136)

አላህ (ሱ.ወ) በርሱ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በቁርኣን እንድናምን አዟል፡፡ ከቁርኣን በፊት በተወረዱ መጽሐፍት ማመንን አዟል፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኢማንን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡ - «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)

የተከበረውን ቁርኣን መፃፍ የሚከናወነው ረቀቅ ባሉ ስርዓቶች መሰረት፣ በብቃትና በጥራት ነው፡፡




በመጽሕፍት ማመን ምንን ያካትታል?



1

ከአላህ በትክክል የተወረዱ በመሆናቸው ማመን

2

የአላህ ቃል (ንግግር) መሆናቸውን ማመን

3

በነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ላይ እንደተወረደው ቁርኣን፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንተወረደው ተውራት፣ በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንደተወረደው ኢንጂል ዓይነት አላህ በስም የጠራቸውን በስማቸው ማመን፡፡

4

ከዜናዎቻቸው፣ በትክክለኛ ዘገባ የደረሱንን በእውነተኝነታቸው ማመን፡፡





የቁርኣን ልዩ መገለጫዎች



የተከበረው ቁርኣን በነብያችንና በአርአያችን በሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የተወረደ የአላህ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም ሙእሚን ይህን” መጽሐፍ በእጅጉ ያልቀዋል፡፡ ድንጋጌዎቹን ለመተግበርና አንቀፆቹን እያስተነተነ ለማንበብ ይጥራል፡፡

ይህ ቁርኣን በቅርቢቱ ዓለም መመሪያችን፣ በመጨረሻው ዓለም የስኬታችን ሰበብ መሆኑ ብቻ ልዩ ለመሆን ይበቃዋል፡፡


የተከበረው ቁርኣን በርካታ መለያዎች አሉት፡፡ ከቀደሙት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚነጥሉት የርሱ ብቻ የሆኑ የተለያዩ መገለጫዎችም አሉት፡፡ ከነኚህም መካከል፡- 

1

የተከበረው ቁርኣን የአምላክን ድንጋጌ ማጠቃለያ የያዘ መሆኑ፡፡ በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ያለውን፣ አላህን በብቸኝነት የመገዛት ትዕዛዝን የሚያጠናክር ኾኖ ነው የመጣው፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በውነት አወረድን» (አል ማኢዳ 48)

«ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ» ማለት በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ከተነገሩ ዜናዎች፣ ከተላለፉ የእምነት አመለካከቶችና ጉዳዮች ጋር የሚስማማና የማይቃረን ማለት ነው፡፡ «በርሱ ላይ ተጠባባቂ» የሚለው ደግሞ ከርሱ በፊት የነበሩ መጽሐት ላይ የሚመሰክርና በአደራ የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡

2

እነሆ የሰው ልጆች በሙሉ በቋንቋና በጎሳ መለያየታቸው እንዳለ ሆኖ፣ ዘመናቸው ምንም እንኳ ከቁርኣን መወረድ በኋላ የመጣ ቢሆንም እርሱን የመከተል፣ እርሱ ያቀፈውን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ቀደምት መጽሐፍት ግን የተወረዱት ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ሕዝቦችና በተወሰነ ዘመን ላይ ነበር፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ (በል)፡፡» (አል አንዓም 19)

3

አላህ (ሱ.ወ) የተከበረውን ቁርኣን የመጠበቁን ኃላፊነት ለራሱ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም የመቀየር፣ የመደለዝ፣ የመከለስና የመበረዝ እጅ አልተሰነዘረበትም፡፡ ወደፊትም ለመቼውም አይዘረጋበትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤ እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡» (አል ሒጅር 9)

ሰለሆነም በውስጡ ያሉ ዜናዎች በሙሉ ትክክለኛ ናቸው፡፡ ልንቀበለውም የግድ ይላል፡፡


ቁርኣንን አስመልክቶ ያለብን ግዴታ ምንድን ነው?
  • ቁርኣንን ልንወድ ይገባል፡፡ ደረጃውን ማላቅና እሱን ማክበርም ይገባል፡፡ እርሱ የፈጣሪ ንግግር ነው፡፡ ከንግግሮች ሁሉ ትክክለኛውና በላጩ እርሱ ነው፡፡
  • ምዕራፎቹንና አንቀፆቹን በማስተንተን እርሱን ዘወትር ማንበብ አለብን፡፡ የቁርኣንን ተግሳጻት፣ ዜናዎችና ታሪኮች ልናሰተነትን ይገባል፡፡ የሕይወታችንን ደካማና ጠንካራ ጎን ለመለየት ሕይወታችንን ለቁርኣን መስጠት አለብን፡፡
  • ድንጋጌዎቹን ልንከተል፣ ትዕዛዛቶቹንና ስርዓቶቹን ልንተገብር፣ እንዲሁም የሕይወታችን መመሪያ ልናደርገው ይገባል፡፡

እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ)፣ ስለ ነብዩ (ስ.ዐ.ወ) ባህሪ በተጠየቁ ጊዜ፣ «ባህሪያቸው ቁርዓን ነበር፡፡ « በማለት መልሰዋል፡፡ (አህመድ 24601/ሙስሊም 746)

የሐዲሱ መልክት፣ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፣ በኑሯቸውና በተግባራቸው የቁርዓንን ድንጋጌና ሕግጋት በመፈፀም የሚያሳዩ እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ በርግጥም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለቁርኣን መመሪያ ሙሉዕ ተከታይነታቸውን አስመስክረዋል፡ ፡ እሳቸው ለእያንዳንዳችን ዓይነተኛ ተምሳሌታችን ናቸው፡ ፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፣ በአላህ መልክተኛ መልካም መከተል አላችሁ፡፡» (አል አህዛብ 21)




በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ስላለ ነገር ሊኖረን የሚገባ አቋም ምንድን ነው?



አንድ ሙስሊም፣ በነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት፣ በነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል፣ በትክክል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡ ሁለቱም በውስጣቸው ለሰው ልጆች ለዚች ዓለምና ለወዲያኛው ዓለም ሕይወታቸው መመሪያና ብርሃን የያዙ፣ ተግሳጻትን እንዲሁም ድንጋጌዎችንና ዜናዎችን አቅፈው የነበሩ መሆናቸውን ያምናል፡፡

ነገር ግን አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ውስጥ የመጽሐፍት ባለቤት የሆኑት አይሁዶችና ክርስቲያኖች፣ መጽሐፍታቸውን እንደበረዙና እንዳበላሹ፣ ከመጽሐፍ ያልሆነን ነገር በውስጡ እንደጨመሩ፣ ከነበረውም እንደቀነሱ ነግሮናል፡፡ በመሆኑም በወረዱበት ይዘት ላይ አልቆዩም፡፡

አሁን ያለው ተውራት፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች አጣመውታል፤ ለውጠውታል፡፡ በርካታ ድንጋጌዎቹን ተጫውተውበታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከነዚያ አይሁዳውያን ከሆኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አሉ፡፡» (አል ኒሳእ 46)

አሁን ያለው ኢንጂልም ቢሆን በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል አይደለም፡፡ ክርስቲያኖችም ኢንጂልን አጣመውታል፡፡ በርካታ በውስጡ የነበሩ ድንጋጌዎችን ለውጠዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ክርስቲያኖችን በማስመለከት እንዲህ ብሏል፡- «ከነሱም እርሱ ከመጽሐፉ ያላደለ ሲኾን ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች አሉ፡፡ እርሱ ከአላህ ዘንድ ያልኾነ ሲኾን እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ ላይ ውሸትን ይናገራሉ፡፡» (አለ ዒምራን 78)

«ከነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተዉ፤ ስለዚህ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው አላህም ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡» (አል ማኢዳ 14)

ዛሬ በመጽሐፍት ባለቤቶች እጅ የሚገኘው፣ ተውራትንና ኢንጂልን አካቷል ብለው የሚያምኑበት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውስጡ በርካታ ብለሹ የእምነት አመለካከቶችንና ትክክለኛ ያልሆኑ ዜናዎችን፣ እንዲሁም የውሸት ትረካዎችን ይዟል፡፡ ስለሆነም ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቁርኣን ወይም ትክክለኛ የሐዲስ ዘገባ እውነትነቱን ያጸደቀውን በስተቀር እውነት ብለን አናምንበትም፡ ፡ ቁርኣንና ሀዲስ ያስተባበሉትን ደግሞ እናስተባብላለን፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነውን በዝምታ እናልፋለን፡፡ እውነት ብለን አናጸድቅም ውሸት ነው ብለንም አናስተባብልም፡፡

እንዲህ ከመሆኑም ጋራ፣ አንድ ሙስሊም እነኚህን መጽሐፍት አያንኳስስም፤ አያራክስም፣ ምክንያቱም ምናልባት በውስጣቸው ያልተበረዘና ያልተለወጠ የአላህ ንግግር ቅሪት ሊኖር ይችላል፡፡

አንድ ሙስሊም ተውራትና ኢንጂል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡ ነገር ግን በርካታ ቅየራዎችና ድለዛዎች የተካሄደባቸው በመሆኑ ከቁርኣንና ከሱና ጋር የሚጣጣመውን እንጂ በውስጣቸው ያለውን አንዱንም እውነት ብሎ አይቀበልም፡፡


በመጽሐፍት የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ


በመጽሐፍት ማመን በርካታ ጥቅሞች ወይም ፍሬዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጥቅሞች መካከል፡

1

አላህ (ሱ.ወ) ከምእመናን ላይ አደጋን በጠቅላላ ይመክታል፡፡ ከመከራና ስቃይ ውስጥ ያወጣቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡» (አል-ሐጅ፡ 38)

2

አላህ በድንጋጌዎቹ ውስጥ ያለውን ጥበብ ወይም ምክንያታዊነት ማወቅ፡፡ ይኸውም ለያንዳንዱ ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚመጥንና ከባህሪው የሚስማማ የሆነ የራሱ ልዩ ድንጋጌ የደነገገለት መሆኑ ነው፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፡» (አል ማኢዳ 48)

3

እነኚህን መጽሐፍት በማውረድ ለተከሰተው የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ፡፡ እነኚህ መጽሐፍት በዱንያም በኣኺራም ብርሃንና መመሪያ ናቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳችን ለዚህ ታላቅ የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡




በመልዕክተኞች ማመን



በመልዕክተኞች ማመን



ለሰው ልጆች ሕግጋትን የሚያብራራላቸውና ወደ ትክክለኛው ጎዳና የሚመራቸው ከጌታ የሆነ መልዕክተኛ ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ መለኮታዊ መልዕክት የዓለም እስትንፋስና የሕይወት ብርሃን ነው፡፡ መንፈስ፣ ሕይወትና ብርሃን የሌለው ዓለም እንዴት ዓይነት ሕልውና ሊኖረው ይችላል?

አላህ (ሱ.ወ) መልክቱን ሩሕ ሲል የሰየመው ለዚህ ነው ፡፡ ሩሕ ከሌለ ሕይወት የለም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እንደዚሁም ወደ አንተ ከትዕዛዛችን ሲኾን መንፈስን (ቁርኣንን) አወረድን፡፡ መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም፡፡ ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው፡፡ አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በርግጥ ትመራለህ፡፡» (አል ሹራ 52)

ይኸውም የሰው ልጅ አዕምሮ በጥቅሉ ጠቃሚና ጎጂ ነገሮችን መለየት የሚችል ቢሆንም፣ በመልዕክተኞች አማካይነት ካልሆነ በስተቀር በረቀቀ መልኩ መጥፎውንና መልካሙን የሚለይበት መንገድ አይኖረውም፡፡

በሁለቱም ዓለም ደስታም ሆነ ስኬት ሊገኝ የሚችልበት መንገድ በመልዕክተኞች እጅ የሚገኘው ብቻ ነው፡፡ ክፉና ደጉንም በረቀቀ መልኩ የሚለየው መንገድ የነርሱ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ፣ መልዕክተኞች ካስተላለፉት መልዕክት ጀርባውን የሰጠ ሰው ለመልዕክቱ ተቃራኒ በሆነበትና ጀርባውን በሰጠበት ልክ አለመረጋጋት፣ ጭንቀትና መረበሽ ያገኘዋል፡፡




በመልዕክተኞች ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡



በመልዕክተኞች ማመን ከስድስቱ የኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «መልዕክተኛው ከጌታው ወደ እርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእመናንም (እንደዚሁ)፤ ሁሉም በአላህ፤ በመላዕክቱም፤ በመጽሐõፍቱም፣ ከመልዕክተኞቹ በአንድም መካከል አንለያይም (የሚሉ ሲሆኑ ) አመኑ፡፡» (አልበቀራ 285)

አንቀጹ፣ በመልዕክተኞች መካከል ምንም ሳይለያዩ በሁሉም ማመን ግዴታ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ አይሁዶችና ክርስቲያኖች እንዳደረጉት በከፊሎቹ አምነን በከፊሎቹ አንክድም፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የኢማን ማዕዘናትን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡- «በአላህ በመላበአላህ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)





በመልዕክተኞች የማመን ትርጓሜ



አላህ (ሱ.ወ) በእያንዳንዱ ሕዝብ ውስጥ ከነርሱው የሆኑ፣ አላህን በብቸኝነት ወደ መገዛት የሚጣሩና ለርሱ ተጋሪ እንደሌለው የሚያስተምሩ መልዕክተኞችን የላከ መሆኑን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ መልዕክተኞች ሁሉም እውነተኞችና እውነተኝነታቸው በአምላክ የተረጋገጠ ነው፡፡ አላህን በእጅጉ የሚፈሩና ታማኞች ናቸው፡፡ ወደ ትክክለኛው ጎዳና የተመሩና የሚመሩ ናቸው፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እነርሱን የላከበትን ነገር በሙሉ አድርሰዋል፡፡ ከርሱ ምንም የደበቁትም ሆነ የቀየሩት ነገር የለም፡፡ ከራሳቸው ዘንድ አንዲትም ፊደል በውስጡ አልጨመሩም አልቀነሱምም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በመልዕክተኞቹም ላይ ግልጽ ማድረስ ብቻ እንጂ ሌላ የለባቸውም፡፡» (አል ነሕል 35)






በመልዕክተኞች ማመን ምንን ያካትታል?



1

መልዕክታቸው በትክክልና በቀጥታ ከአላህ ዘንድ ነው የተላለፈው ብሎ ማመን፡፡ የመልዕክተኞች ሁሉ ጥሪ፣ አላህን ያለአጋር በብቸኝነት ወደ ማምለክ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በየ ሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል::» (አል ነህል 36)

በርግጥ የየነብያቱ ደንብና ስርዓት ንዑስ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊለያይ ይችላል፡፡ ከነኚያ ከተላኩባቸው ሕዝቦች አንጻር የተፈቀዱና የተከለከሉ ነገሮች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ለሁሉም ህሕግና መንገድን አደረግን፡፡» (አል ማኢዳ 48)

2

በነብያትና በመልክተኞች በሙሉ ማመን፡፡

 አላህ በስማቸው የነገረንን ከነስማቸው እናምንባቸዋለን፡፡ ለምሳሌ ሙሐመድ፣ ኢብራሒም፣ ሙሳ፣ ዒሳ፣ ኑሕ (ዐለይሂሙ ሰላም) …. ከነሱ መካከል ስማቸውን የማናውቃቸውን ደግሞ በጥቁሉ እናምንባቸዋለን፡፡ ከነሱ መካከል አንዱን የካደ ሁሉንም ክዷል፡፡

3

በቁርኣንና በሐዲስ የተጠቀሱ የመልዕክተኞችን ገድልና ተዓምራት እውነት ነው ብሎ መቀበል፡፡ ለምሳሌ ለነብዩላህ ሙሳ (ዐ.ሰ) ባሕሩ የተሰነጠቀላቸው መሆኑን ማመን፡፡ 

4

ወደ እኛ የተላኩትን መልዕክተኛ ህግና ስርዓት መተግበር፡፡ እሳቸውም ከሁሉም በላጩና መቋጫ የሆኑት ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ 


የመልዕክተኞች መገለጫ
1

የመልዕክተኞች መገለጫ

በነሱና በሌላው ሰው መሐከል ያለው ልዩነት፣ አላህ (ሱ.ወ) በመለኮታዊ ራዕይና መልዕክት የመረጣቸው መሆኑ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከአንተም በፊት ወደ እነሱ የምናወርድላቸው የኾኑ ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም፡፡» (አል አንቢያእ 7) 

የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ደረጃ የላቸውም፡፡

ነገር ግን በውጫዊ ተክለ ሰውነታቸው ምንም እንከን የሌላቸው፣ የሙሉዕነትን ደረጃ የደረሱ ሲሆን በስነምግባራቸውም በሙሉዕነት የመጨረሻውን ጣራ የነኩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በጎሳቸውም የተከበረ ጎሳ አባል ናቸው፡፡ እንዲሁም ብሩህ አዕምሮና ማራኪ ልሳን የተቸሩ ናቸው፡፡ ይህም የመልዕክቱን ውጣ ውረድ በአግባቡ እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል፡፡ የነብይነትን ፈተናም በብቃት እንዲወጡ አግዟቸዋል፡፡ 

አላህ (ሱ.ወ) መልዕክተኞችን ከሰው ዘር ያደረገበት ምክንያቱ የሰዎች ተምሳሌቶች ከራሳቸው እንዲሆን ነው፡፡ በመሆኑም መልዕክተኞችን መከተልና እነርሱን በተምሳሌትነት መያዝ በሰዎች ሊከናወን የሚችልና በችሎታቸው ስር ያለ ጉዳይ ነው፡፡

2

አላህ (ሱ.ወ) መልዕክቱን በማስተላለፉ ለይቷቸዋል፡፡

ከሌላው ሰው ነጥሎ እነርሱን መለኮታዊ ራዕዩን እንዲረከቡ መርጧቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደ እኔ የሚወረድልኝ ቢጢያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፡፡» (አል ካሕፍ 110) የነብይነት ማዕረግም ሆነ መለኮታዊ መልዕክት፣ በመንፈሳዊ ምጥቀት ወይም በጮሌነት ወይም በአዕምሮ ብስለት የሚያገኝ ነገር አይደለም፡፡

እሱ የአላህ መምረጥና ማጨት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከሰዎች መካከል መልዕክተኞችን መርጦ አጭቷቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ መልክቱን የሚያደርግበትን ስፍራ ዐዋቂ ነው፡፡» (አል አንዓም 124)

3 እነርሱ ከአላህ በሚያስተላልፉት መልዕክት ከስህተትና ከመርሳት የተጠበቁ ናቸው፡፡ ከአላህ በሚያስተላልፉት መልዕክት አይሳሳቱም፡፡ አላህ ወደ እርነሱ የላከውንም በማስፈፀም አይሳሳቱም፡፡
4

እውነተኝነት፡

መልዕክተኞች በንግግራቸውም በተግባራቸውም እውነተኞች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ይህ አዛኙ ጌታ የቀጠረን፣ መልዕክተኛቹም እውነትን የነገሩን ነው፡፡» (ያሲን 52)

5

ትዕግስት፡

መል°ክተኞች ወደ አላህ ሃይማኖት አብሳሪና አስጠንቃቂ በመሆን በርግጥ ተጣርተዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ ስቃዮችና መከራዎች ደርሰውባቸዋል፡፡ ሁሉንም የሚደርስባቸውን መከራና ስቃይ የአላህን ቃል የበላይ በማድረግ ጉዞ ላይ በትዕግስት ተሸክመው አልፈዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከመልዕክተኞችም የቆራጥነት ባለቤት የነበሩት እንደታገሱ ሁሉ ታገስ፡፡» (አል አሕቃፍ 35)



የመልዕክተኞች ምልክቶችና ታዓምራታቸው



አላህ (ሱ.ወ) መልዕክተኞቹን በማስረጃና ተያያዥነት ባላቸው የተለያዩ ነገሮች እውነተኝነታቸውንና ነብይነታቸውን በማረጋገጥ ረድቷቸዋል፡፡ ከዚህም መካከል በሰው ልጅ ችሎታ የማይከሰቱ በሆኑ ታዓምራትና ግልጽ በሆኑ ምልክቶች ያደረገላቸው እገዛ ወይም ድጋፍ አንዱ ነው፡፡ ይህም የሆነው እውነተኝነታቸውን ለማጽደቅና ነብይነታቸውን ለማጽናት ነው፡፡

ታዓምራት የሚባለው ተለምዶን ጥሰው የሚከሰቱ ነገሮችን ነው፡፡ ይኸውም አላህ (ሱ.ወ) በነብያቱና በመል°ክተኞቹ አማካይነት ይፋ የሚያደርገው ሲሆን ሰዎች መሰሉን ሊያመጡ ወይም ሊያስከስቱ የማይችሉት እንደሆነ በመፎካከር መልክ የሚከሰት ነው፡፡

ከነብያት ተዓምራት መካከል፡

  • የነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) በትር ወደ እባብነት መቀየር፡
  • ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ሕዝቦቻቸው በቤቶቻቸው ውስጥ ስለሚመገቡትና ስለሚያከማቹት ምግብ መናገራቸው፡
  • ለነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጨረቃ መሰንጠቅ:



በዒሳ(ዐ.ሰ) ዙሪያ ያለው የሙስሊም እምነት



1

እርሱ ዒሳ(ዐ.ሰ) ከታላላቅ መልዕክተኞች አንዱና ስብዕናው እጅግ የላቀ ነው፡፡ እነኚህ ከመልዕክተኞች መካከል ስብዕናቸው እጅግ የላቀ ነቢያት የቆራጥነት ባለተቤት በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነርሱም ሙሐመድ’ ኢብራሒም’ ኑሕ’ ሙሳና ዒሳ ናቸው (አለይሂሙ ሰላም)፡ ፡ አላህ (ሱ.ወ) በሚከተለው ቃሉ ዘክሯቸዋል፡- «ከነብዮችም የጠበቀ ቃልኪዳናቸውን በያዝን ጊዜ (አስታውስ)፤ ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሂምም፣ ከሙሳም፣ ከመርየም ልጅ ዒሳም(በያዝን ጊዜ አስታውስ)» (አል አሕዛብ 7) ይላል፡፡

2

ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) የኣደም ዝርያ ሰው ነው፡፡ 

አላህ (ሱ.ወ) ወደ ነገደ ኢስራኢል የላከው ሲሆን የተለያዩ ተዓምራት በርሱ እጅ እንዲፈፀሙ አድርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ደረጃ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለኢስራኢልም ልጆች ታምር ያደረግነው የሆነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ » (አል ዙኽሩፍ 59)

ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ሕዝቦቹን፣ እሱንም ሆነ እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው እንዲይዟቸው ፈፅሞ አላዘዘም፡፡ ለነርሱ ያላቸው አላህ ያዘዘውን ብቻ ነበር፡፡ «ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ» (አል ማኢዳ 117)

3

እሱ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡

እናቱ መርየም፣ ፃድቅ፣ እውነተኛ፣ ለጌታዋ ፍፁም ታዛዥና ተገዢ፣ ጥብቅ፣ ጨዋና ድንግል ሴት ነች፡፡ ዒሳን(ዐ.ሰ) የፀነሰችው ያለአባት በአላህ (ሱ.ወ) ችሎታ ነው፡፡ የእርሱ አፈጣጠር ዘልዓለማዊ ተዓምር ነው፡፡ ልክ ኣደምን ያለአባት እና ያለእናት እንደፈጠረው ሁሉ እርሱንም ያለ አባት ፈጠረው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ ኣደም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ሁን አለው ሆነም፡፡» (አል ዒምራን 59)

4

በርሱ በዒሳ(ዐ.ሰ) እና በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መሐከል የተላከ መልዕክተኛ የለም፡፡ ስለ ነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትንቢት ተናግሮ አብስሯል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የመርየም ልጅ ዒሳም፡ የኢስራኢል ልጆች ሆይ! እኔ ከበፊቴ ያለውን ተውራትን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደ እናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ (አስታውስ) በግልጽ ታዕምራት በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልጽ ድግምት ነው አሉ፡፡» (አሥ ሠፍ 6) 

5

አላህ (ሱ.ወ) በእርሱ እጅ እንዲፈፀሙ ባደረጋቸው ታዓምራት እናምናለን፡፡ ለምፃምን ማዳኑን፣ አይነ ስዉራን ማብራቱን፣ ሙታንን ማስነሳቱን፣ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ስለሚበሉትና ስለሚያከማቹት መናገሩን እናምናለን፡፡ ሁሉም በአላህ ፍቃድ የተፈፀሙ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ለነብይነቱና ለመልዕክተኝነቱ ትክክል ለመሆኑ ግልጽ የሆነ ማስረጃ አድርጎታል፡፡ 

6

ዒሳ(ዐ.ሰ) የአላህ ባሪያና መልክተኛ ነው ብሎ እስከሚያምን ድረስ የአንድም ሰው ኢማን የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ አይሁዶች እርሱን ከገለጹበት የቅጥፈትና ፀያፍ ነገሮች ሁሉ የጸዳና የጠራ እንደሆነም እናምናለን፡፡

በዒሳ እውነተኛ ማንነት ዙሪያ የተሳሳቱትን የክርስቲያኖች አመለካከትም እናወግዛለን፡፡ ይኸውም እሱና እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት ማድረጋቸው ነው፡፡ ከፊላቸው እርሱ የአላህ ልጅ ነው ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ ከስላሴዎች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ አላህ እነርሱ ከሚሉት ሁሉ የላቀ ነው፡፡ 

7

አላህ (ሱ.ወ) አይሁዶች ዒሳን(ዐ.ሰ) ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ ወደ ሰማይ ከፍ አደረገውና አሳረገው እንጂ እሱ አልተገደለም አልተሰቀለምም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የእርሱ ምስል በሌላ ሰው ላይ እንዲሆን አደረገ እናም ያንን ሰው ዒሳ መስሏቸው ገደሉት ሰቀሉትም፡ ፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸውም (ረገምናቸው) አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡ ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም በትንሳኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡ » (አል ኒሳእ 157-159)

አላህ (ሱ.ወ) እርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ እንዲያርግ በማድረግ ጥበቃ አድርጎለታል፡፡ በመጨረሻው ዘመን ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ሕግና ስርዓት ይዳኛል፡፡ ከዚያም በዚ‹ ምድር ይሞታል፤ በሷም ውስጥ ይቀበራል፡ ፡ ሌሎች ሰዎች እንደሚቀሰቀሱት የትንሳኤ ቀን ይቀሰቀሳል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከርሷ (ከምድር) ፈጠርናችሁ በርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን ከርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን፡፡» (ጧሃ 55)

የአቅሷ መስጂድ ሙስሊሞች ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ በምድር ላይ ከሐረም መስጂድ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተሰራ መስጂድ ነው፡፡ ነብያችን(ሰ.ዐ.ወ) እና የተቀሩት ነብያትም በውስጡ ሰግደዋል፡፡




በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነትና መልዕክተኝነት ማመን



  • ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን እናምናለን፡፡ እርሳቸው የመጀመሪያዎችም የኋለኞችም አለቃና የነብያት መቋጫ ናቸው፡፡ ከርሳቸው ብኋላ የሚነሳ ነብይ የለም፡፡ መልዕክታቸውን አድርሰዋል፡፡ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሕዝባቸውን መክረዋል፡፡ በአላህ መንገድ መታገል የሚገባቸውን ያክል ታግለዋል፡፡ 
  • እርሳቸው የተናገሩትን በሙሉ እንቀበላለን፡፡ ያዘዙትን እንተገብራለን፡፡ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር እንርቃለን፡ ፡ እርሳቸው በዘረጉልን መስመር መሰረት አላህን እንገዛለን፡፡ ከርሳቸው ባሻገር ማንንም በአርዓያነት አንከተልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አላችሁ፡፡» (አል አሕዛብ 21) 
  • ለወላጅ፣ ለልጅ፣ በአጠቃላይ ለሰዎች ካለን ውዴታ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ውዴታ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል፡ ፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «አንዳችሁም እኔ እርሱ ዘንድ ከወላጆቹ፣ ከልጆቹና ከሰዎች በሙሉ የበለጠ ተወዳጅ እስካልሆንኩ ድረስ አያምንም፡፡» (አል ቡኻሪ 15/ ሙስሊም 44) እርሳቸውን በትክክል መውደድ ማለት ፈለጋቸውን መከተል፣ መመሪያቸውን መንገድ ማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛ ደስታም ሆነ ሙሉዕ መመራት ሊረጋገጥ የሚችለው እርሳቸውን በመታዘዝ ብቻ ነው፡ ፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ብትታዘዙትም ትመራላችሁ፤ በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም፡፡» (አል ኑር 54) 
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተላለፉትን በሙሉ መቀበል አለብን፡፡ ለፈለጋቸውም ታዛዦች መሆን ይኖርብናል፡፡ የእርሳቸውን መመሪያ ትልቅ ስፍራና ክብር ልንቸረው ያስፈልጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍፁም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፡፡» (አል ኒሳእ 65)
  • የእርሳቸውን ትዕዛዝ ከመጻረርና ከመቃረን ልንጠቀቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የርሳቸውን ትዕዛዝ መቃረን ለፈተና፣ ለጥመትና ለአሳማሚ ቅጣት ይዳርጋል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ» (አል ኑር 63) 



የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ልዩ ይዘት


የነብዩ ሙሐመድ መልክት ከቀደምት መልዕክቶች ለየት የሚያደርጉት በርካታ ይዘቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት የቀደምት መልዕክቶችን መልዕክት የሚቋጭ መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፡፡ ግን የአላህ መልዕክተኛና የነብዮች መደምደሚያ ነው፡፡» (አል አሕዛብ 40) 
  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ቀደምት መልዕክቶችን የተካ መሆኑ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከተላኩ ብኋላ አላህ (ሱ.ወ) እርሳቸውን ከመከተል ውጭ ምንም ዓይነት ሃይማኖትን አይቀበልም፡ ፡ በርሳቸው ጎዳና እንጂ አንድም ሰው ወደ ጀነት ጸጋ መድረስ አይችልም፡፡ እርሳቸው ከመልዕክተኞች ሁሉ የተከበሩ ናቸው፡፡ ሕዝባቸውም ከሕዝቦች ሁሉ ምርጥና በላጭ ሕዝብ ነው፡፡ ሕግጋታቸውም ከሕግጋት ሁሉ የተሻለና የተሟላ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡» (አል ዒምራን 85) 
    ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፡ ከዚህ ሕዝብ ውስጥ የሁድም ሆነ ክርስቲያን አንድም ሰው ስለኔ ሰምቶ በተላኩበት የማያምን አይኖርም ከእሳት ጓዶች ቢሆን እንጂ» (ሙስሊም 153 / አህመድ 8609) 
  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልክት ሁለቱንም ፍጡሮች ማለትም አጋንንትንም ሰውንም የሚመለከት መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጅኖች ያሉትን ሲያወሳ እንዲህ ብሏል፡- «ወገኖቻችን ሆይ የአላህን ጠሪ ተቀበሉ፡፡»
    (አል አሕቃፍ 31) « አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢኾን እንጂ አልላክንህም ፡ ፡» (ሰበእ 28)

    ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በስድስት ነገሮች ከነብያት ተልቄያለሁ፡ ጥቅላዊ የንግገር ስልትን ተሰጥቻለሁ፤ ጠላትን በማስፈራት ታግዣለሁ፣ ምርኮ ተፈቅዶልኛል፣ ምድር ንፁሕና የጸሎት ስፍራ ተደርጋልኛለች፣ ወደ ፍጡራን በመሉ ተልኬያለሁ፣ ነብያት በእኔ ተደምድመዋል፡፡» (አል ቡኻሪ 2815 / ሙስሊም 523)



በመልዕክተኞች የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ


በመልዕክተኞች ማመን ከባድ ጥቅም አለው ከነዚህም መካከል

1

አላህ(ሱ.ወ0 ለባሮቹ ያለውን ርህራሄና እንክብካቤ ማወቅ፡

ይኸውም መልዕክተኞቹን ወደ ነርሱ በመላክ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና እንዲመሯቸውና በምን መልኩ አላህን ማምለክ እንዳለባቸው እንዲያብራሩላቸው በማድረጉ ነው፡፡ የሰው ልጅ አዕምሮ ይህን የማወቅ ችሎታ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ስለ ነብያችን ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- «(ሙሐመድ ሆይ) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡» (አል አንቢያእ 117)

2

በዚህ ታላቅ ጸጋው ላይ አላህን ማመስገን

3

መልዕክተኞችን መውደድ፣ ማላቅና ለነሱ በሚገባ መልኩ እነሱን ማድነቅና ማሞገስ፡፡ ምክንያቱም እነሱ አላህን በመገዛት፣ መልዕክቱን በማድረስና ለባሮቹ መልካምን በማስተማር ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋልና ነው፡፡

4

መልዕክተኞች ከአላህ ዘንድ የተላኩበትንና ይዘው የመጡትን መልዕክት መከተል፡

እሱም አላህን በብቸኝነት ማምለክና ለርሱ ተጋሪ አለማድረግ ነው፡፡ እርሱንም በተግባር መተርጎም ነው፡፡ በዚህም ምእመናን በሁለቱም ዓለም መመራትን ስኬትንና መልካሙን ሁሉ ያገኛሉ፡፡ 

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገረምም፡፡ ከግሳጼዬም የዞረ ሰው ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፡፡» (ጧሃ 123-124)


የአቅሷ መስጂድ ሙስሊሞች ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ በምድር ላይ ከሐረም መስጂድ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተሰራ መስጂድ ነው፡፡ ነብያችን(ሰ.ዐ.ወ) እና የተቀሩት ነብያትም በውስጡ ሰግደዋል፡፡


በመጨረሻው ቀን ማመን



በመጨረሻው ቀን የማመን ትርጓሜ



አላህ (ሱ.ወ) ሰዎችን ከቀብር ይቀሰቅሳል ከዚያም በስራዎቻቸው ይተሳሰባቸዋል በዚያም ይመነዳቸዋል፤ በዚህም የጀነት ነዋሪዎች በማረፊያቸው ይረጋሉ፤ የእሳት ነዋሪዎችም በማረፊያቸው ይረጋሉ፤

ብሎ በቁርጠኝነት ማመን ነው፡፡

በመጨረሻው ቀን ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡ በርሱ ሳያምኑ ኢማን ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ግን መልካም ስራ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው ነው»» (አል በቀራ 177) 



ቁርኣን በመጨረሻው ቀን በማመን ላይ ትኩረት ያደረገው ለምንድን ነው?



ቁርኣን በመጨረሻው ቀን በማመን ላይ ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በየአጋጣሚው ሁሉ ስለሱ አሳስቧል፡ ፡ በተለያየ የዐረበኛ አገላለጾች የርሱን ተከሳችነት አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመጨረሻው ቀን ማመንን በአላህ ከማመን ጋር አስተሳስሮታል፡፡

ምክንያቱም በአላህና በፍትሃዊነቱ ማመን በመጨረሻው ቀን ማመንን ያስገድዳል፡፡ የዚህ ማብራሪያም እንደሚከተለው ይሆናል፡-

አላህ (ሱ.ወ) በደልን አይቀበልም፡፡ በዳይን ሳይቀጣ፣ ተበዳይንም ሳይክስ አይተውም፡፡ መልካም ሰሪን ሳይመነዳና ሳይከፍለው አይቀርም፡፡ ሁሉንም ባለ መብት የሚገባውን መብት ይሰጠዋል፡፡ በዚች ዓለም ላይ በዳይ ሆኖ የሚኖር፣ በዳይ ሆኖ የሚሞት፣ ነገር ግን ምንም የማይቀጣ ሰው እንመለከታለን፡፡ በተቃራኒው ተበዳይ ሆኖ የሚኖር ተበዳይ ሆኖ የሚሞት ግን አንድም መብቱ የማይመለስለት ሰው እናያለን፡፡ ታዲያ አላህ በደልን አይቀበልም የሚለው ትርጓሜ ምንድነው? ትርጓሜው ከዚህ ሕይወት ሌላ እኛ ዳግም የምንኖርበት ሌላ ሕይወት አለ ማለት ነው፡፡ የግድ ሌላ የምላሽ ሕይወት ይኖራል፡፡ መልካም ሰሪ የሚመነዳበት፣ መጥፎ የሰራም የሚቀጣበት፣ ሁሉም ባለ መብት የሚገባውን መብት የሚያገኝበት ዓለም ይኖራል፡፡

ኢስላም ግማሽ የቴምር ፍሬን በመለገስ እንኳን ቢሆን ለሌሎች መልካም በመዋል ከእሳት እንድንርቅ ያዘናል፡፡



በመጨረሻው ቀን ማመን ምንን ያካትታል?



አንድ ሙስሊም በመጨረሻው ቀን ማመኑ በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ ያካትታል፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል፡- 

1

በመቀስቀስና በመሰብሰብ ማመን፡- ሙታን ከመቃብራቸው ወጥተው ሕያው እንዲሆኑ ይደረጋሉ ፡፡ ሩሐቸውም ወደየገላዎቻቸው ይመለሳሉ፡፡ ሰዎች የዓለማት ጌታ ፊት ይቆማሉ፡፡ ከዚያም ጫማ ሳይጫሙ እርቃናቸውን ልክ መጀመሪያ ሲፈጠሩ እንደነበሩት ሆነው በአንድ ስፍራ ይሰበሰባሉ፡፡ 

በመቀስቀስ ማመን በቁርኣንና በሐዲስ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ ጤናማ አዕምሮና የተፈጥሮ ባህሪም ያጸደቁት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጠኝነት አላህ (ሱ.ወ) በቀብሮች ውስጥ ያለን እንደሚቀሰቅስ፣ ነፍሶች ወደየገላዎቻቸው እንደሚመለሱ፣ ሰዎች በጠቅላላ የዓለማት ጌታ ፊት እንደሚቆሙ እናምናለን፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከዚያም እናንተ ከዚህ በኋላ በእርግጥ ሟቾች ናችሁ፡፡ ከዚያም እናንተ በትንሳኤ ቀን ትቀሰቀሳላችሁ፡፡» (አልሙዕሚኑን 15-16)

መለኮታዊ መጽሐፍት በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) ጥበበኝነት በውስጡ ያዘለውም ይህንኑ ነው፡፡ ይኸውም አላህ (ሱ.ወ) በተጣለባቸው በእያንዳንዱ ኃላፍነት ፍጡራን የሚመነዱበት የሆነ መመለሻ ዓለም እንዳዘጋጀ በመልክተኞቹ ልሳን መናገሩ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን፣ እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)» (አል ሙዕሚኑን 115)


መቀስቀስን የሚያረጋግጡ የቁርኣን ማስረጃዎች

  • የሰው ልጅን ያለ አንዳች ቀዳሚ ምሳሌ የፈጠረው አላህ ነው፡፡ ያለ አንዳች ቀዳሚ ምሳሌ የፈጠረ ደግሞ መልሶ ማስገኘት፣ ወደነበረበት መመለስ አይሳነውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱም ያ መፍጠርን የሚጀምር ከዚያም የሚመልሰው ነው፡፡» (አል ሩም 27)  
    አላህ (ሱ.ወ) አጥንቶች ከበሰበሱ በኋላ እንደነበሩ መመለሳቸውን ለሚያስተባብል ሰው ምላሽ እንዲሰጥበት ሲያዝ እንዲህ ብሏል፡- « ያ በመጀመሪያ ጊዜ ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፤ እርሱም በፍጡሩ ሁሉ(ኹኔታ) ዐዋቂ ነው በለው፡፡» (ያሲን 79) 
  • ምድር ምንም ዓይነት ዛፍም ሆነ አረንጓዴ ተክል የማይታይባት ኾና ከደረቀችና ከሞተች በኋላ፣ አላህ (ሱ.ወ) ዝናብ ያወርድባታል፡፡ እንደ አዲስ በአረንጓዴ ትሸፈናለች፡፡ ከእያይነቱ ቡቃያን ታበቅላላች፡፡ እናም ምድርን በዚህ መልኩ ሕያው ማድረግ የቻለ ጌታ ሙታንንም ሕያው ማድረግ ይችላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፤ በርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን፡ ፡ ዘምባባንም ረዣዥም ለርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትሆን (አበቀልን) ለባሮቹ ሲሳይ ትኾን ዘንድ (አዘጋጀናት) በርሱም የሞተችን አገር ሕያው አደረግንበት (ከመቃብር) መውጣትም እንደዚሁ ነው፡፡» (ቃፍ 9-11) 
  • ማንኛውም ማገናዘብ የሚችል ሰው የሚረዳው ነገር ቢኖር አንድ ትልቅና ከባድን ነገር መከወን የቻለ ከሱ በታች የሆነን ነገር በሚገባ መከወን እንደሚችል ጥርጥር የሌለው መሆኑን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እጅግ በጣም ግዙፍ፣ ሰፋፊ፣ ውስብስብና ድንቅ ፍጥረቶች ከመሆናቸው ጋር ሰማያትን፣ ምድርንና ከዋክብትን ያለ አንዳች ቀዳሚ ናሙና ፈጥሯቸዋል፡፡ በመሆኑም የበሰበሱ አጥንቶችን ሕያው በማድረግ ቻይ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ እርሱም በብዙ ፈጣሪና ዐዋቂው ነው፡፡» (ያሲን 81) 



2

በምርመራና በሚዛን ማመን፡ አላህ (ሱ.ወ) ፍጡራኑን በዱንያ ሕይወት ሲሰሩት በነበረው ስራቸው ይመረምራቸዋል፤ ይተሳሰባቸዋል፡፡ የአሃዳዊነት፣ የተውሂድ አራማጆች የሆኑ፣ አላህንና መልክተኛውን የሚታዘዙ፣ ምርመራቸው እጅግ በጣም ገር ነው፡፡ ከአጋሪያን የሆነ አመጸኛ ደግሞ ምርመራው እጅግ በጣም ብርቱ ነው፡፡

ስራዎች ትልቅና ከባድ በሆነ ሚዛን ይመዘናሉ፡ ፡ መልካም ስራዎች በአንድ ጎን፣ ክፉ ስራዎች ደግሞ በሌላኛው ጎን ይደረጋሉ፡፡ የመልካም ስራው ክብደት ከመጥፎው ስራው የበለጠና ሚዛን የደፋለት ከጀነት ሰዎች ይሆናል፡፡ የመጥፎ ስራው ክብደት ከመልካም ስራው የበለጠና ሚዛን የደፋበት ደግሞ ከእሳት ሰዎች ይሆናል፡፡ ጌታህ ማንንም አይበድልም፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በትንሳኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፡፡ (ስራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ፡፡» (አል አንቢያእ 47)

3

ጀነትና እሳት፡ ጀነት የዘልዓለማዊ ጸጋዎች ዓለም ናት፡፡ ጀነት አላህ (ሱ.ወ) እርሱን ለሚፈሩ፣ እሱና መልክተኛውን ለሚታዘዙ ምዕመናን ያዘጋጃት ናት፡፡ በውስጧ ነፍሶች የሚፈልጉት ዘውታሪ የሆኑ የጸጋ ዓይነቶች በሙሉ አሉ፡፡ በሷ ውስጥ የሚወደዱ ነገሮች ሁሉ የዓይን መርጊያዎች ሲሆኑ ይገኛሉ፡፡ 

አላህ (ሱ.ወ) የጎን ስፋቷ ብቻ የሰማያትና የምድርን ያክል የሆነችውን ጀነት ለመግባት በታዛዥነት ላይ ባሮቹ እንዲሸቀዳደሙ ሲያነሳሳና ሲያበረታታ እንዲህ ብሏል፡- «ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ፡፡» (አለ ዒምራን 133)

እሳት ደግሞ ዘልዓለማዊ መቀጫ ዓለም ናት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለካሃዲያን፤ ለነዚያ በአላህ ለካዱና መልክተኞች ላይ ላመጹት መቀጫ ትሆን ዘንድ ያዘጋጃት ናት፡፡ በውስጧ በአዕምሮ ውልብ ብሎ የማያውቅ፣ እጅግ በጣም አሳማሚ ቅጣት፣ ስቃይ፣ ሰቆቃና መከራ አለ፡፡

አላህ (ሱ.ወ) ባሮቹን ከዚች ለከሃዲያን መቀጫ ካዘጋጃት እሳት በማስጠንቀቅ መልክ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጊያዎች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፡ ለከሃዲዎች ተደግሳለች፡፡ » (አል በቀራ 24)

አምላካችን ሆይ ጀነትንና ከንግግርም ከስራም ወደርሷ የሚያቃርበውን እንድትለግሰን እንጠይቅሃለን፡፡ ከእሳትና ወደርሷ ከሚያቃርብ ንግግርና ስራም ባንተ እንጠበቃለን፡፡

4

የቀብር ስቃይና ድሎቱ፡ ሞት እውነት መሆኑን እናምናለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ፡፡» (አል ሰጅዳ 11) 

ይህ በተጨባጭ የሚመለከቱት፣ ጥርጥር የሌለው እውነታ ነው፡፡ የሞተ ወይም የተገደለ ብቻ በማንኛውም ሁኔታ ሕይወቱ ያለፈ ሰው፣ ይህ ቀነ ገደቡ እንደሆነና የሞተበት ሁኔታ ከዕድሜው ላይ ምንም እንደማያጎድል እናምናለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለሕዝብም ሁሉ የተሰነ ጊዜ አላቸው፡ ፡ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት አንዲትን ሰዓት አይቆዩም (ከጊዚያቱም) አይቀድሙም፡፡» (አል አዕራፍ 34)

• አንድ የሞተ ሰው ቂያማው ቆማበታለች፡፡ ወደ ወዲያኛው ዓለምም ተሸጋግሯል፡፡

• ለከሃዲያንና ለአማጽያን በቀብር ውስጥ ቅጣት እንደተዘጋጀ፣ ለምእመናንና ለጻድቅ ባሮች ደግሞየድሎት ጸጋዎች እንደተደገሱ የሚያረጋግጡ በርካታ ሐዲሶች ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተዘግበዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ እናምናለን፡፡ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አንፈላፈልም፡፡ ምክንያቱም ይህ የስውሩ ዓለም ክስተትና አዕምሮ ተጨባጭ ሁኔቴውንና በምን ዓይነት እንደሚከሰት ሊደርስበት ስለማይችል ነው፡፡ ልክ እንደ ጀነትና እሳት የስዉሩ ዓለም ክስተት እንጂ የይፋዊ ዓለም ክስተት አይደለም፡፡ አዕምሮ ሊቀይስ፣ ሊመረምርና ሊወስን የሚችለው በነባራዊው ዓለም ተመሳሳይ ያለውንና የርሱን ስርዓት የሚከተልን ነገር ብቻ ነው፡፡

• የቀብር ሕይወት በስሜት ሕዋሳት የሚደረስበት አይደለም፡፡ ስውር ወይም ገይብ ሕይወት ነው፡፡ በሕዋስ የሚደረስበት ቢሆን ኖሮ በስውር ወይም ከሕዋስ በራቀ ነገር ማመንን ጥቅም አልባ ያደርገው ነበር፡፡ ኃላፊነት የተጣለበትንም ሚስጥር ፉርሽ ያደርጋል፡፡ ሰዎችም ባልተቀበሩ ነበር፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «አትቀባበሩም ማለትን ባልሰጋ ኖሮ አላህን እኔ የምሰማወን የቀብር ቅጣት እንዲያሰማችሁ እለምነው ነበር፡፡» (ሙሰሊም 2868 /አል ነሳኢ 2958)

ከላይ የጠቀስነው ምክንያቶች በእንሳሳት ላይ ሰለሌሉ እነሱ ይህን እንዲሰሙ ተደርገዋል፡፡ 



በመጨረሻው ቀን የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ


1

በመጨረሻው ቀን ማመን ሰዎችን በመልካም ስራ ላይ ስርዓት ይዘው እንዲዘወትሩ አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ እንዲሁም አላህን እንዲፈሩና ከሁሉ ለኔ ባህሪና ከይዩልኝ እንዲርቁ በማድረግ የጎላ ሚና አለው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ መልካም ስራ በመጨረሻው ቀን ከማመን ጋር ተያይዞ የሚቀርበውም ለዚህ ነው ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የአላህን መስጂዶች የሚሰራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ነው፡፡»

(አል ተውባ 18) «እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የሚያምኑት እነርሱ በሶላታቸው ላይ የሚጠባበቁ ሲኾኑ በርሱ ያምናሉ፡፡ » (አል አንዓም 92)

2

በሕይወት ውጣውረድ እራሳቸውን በመወጠር አላህን በመታዘዝ ላይ ከመሽቀዳደም ለተዘናጉ፣ ወደ አላህ በመቃረብ ጊዜን ከመሻማት፣ እርሱን ከመታዘዝ፣ የዚችን ዓለም እውነተኛ ገጽታና አጭርነት ከማስተንተን፣ የወዲያኛውን ዓለም መርጊያነት ዘልዓለማዊነት ከማሰብ ለተዘናጉና ለረሱ ማሳሳቢያና ማስጠንቀቂያ አለበት፡፡

አላህ (ሱ.ወ)በቁርኣን ውስጥ መልዕክተኞችን ስራቸውን በመጥቀስ ሲያወሳ፣ እነዚያን ስራዎችና የላቁ ገድሎች እንዲፈጽሙ ሰበብ የሆናቸውን ጉዳይ በማሞገስ ነበር ያወሳው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ ጥሩ በኾነች ጠባይ መረጥናቸው (እርሷም) የመጨረሻይቱን አገር ማስታወስ ናት፡፡» ማለትም የነኚያ የተከበሩ ስራዎቻቸው መንስኤ እነርሱ የመጨረሻይቱን አገር በማስታወስ ለየት ያሉ መሆናቸው ሲሆን ይህም ማስታወሳቸው እነዚያን ስራዎችና አቋሞች እንዲኖራቸው ገፋፍቷቸዋል፡፡

እነርሱን ለማሳሰብና ለማስጠንቀቅ እንዲህ አለ፡- «የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን? የቅርቢቱ ሕይወት በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡» (አል ተውባ 38)

የሰው ልጅ በመጨረሻው ቀን በትክክል በሚያምን ጊዜ ማንኛውም የዚች ዓለም ጸጋ ከመጨረሻው ዓለም ጸጋ ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል እርግጠኛ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በወዲያኛው ዓለም ለአንዲት ቅጽበት የሚያገነውን ቅጣት ምንም ሊያክለው አይችልም፡፡ በዚህም በዱንያ ላይ ያለ የቅጣት ዓይነትም ከመጨረሻው ዓለም ቅጣት ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል ይገነዘባል፡፡ በሌላ በኩል እዚህ ያለ ተድላና ደስታ በወዲያኛው ዓለም ከሚያጋጥም የቅጽበት ጸጋ ወይም ድሎትና ደስታ ጋር አይስተካከልም፡፡

3

የሰው ልጅ በመጨረሻው ቀን ካመነ የስራውን ምንዳ ማግኘቱ አይቀሬ እንደሆነ እርግጠኛ ስለሚሆን ይረጋጋል፡፡ ስለሆነም የሆነ የዚህች ዓለም ጥቅም ቢያመልጠው ወይም ቢያጣው ተስፋ በመቁረጥና በመበሳጨት ነፍሱን በሐዘን አይገድልም፡፡ እንዳውም ታታሪ ሊሆንና አላህ (ሱ.ወ) የመልካም ሰሪን ምንዳ በከንቱ እንደማያስቀር እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ የጎመን ዘር ቅንጣትን የሚያህል ነገር ከርሱ በግፍ ወይም ያለ አግባብ ቢወሰድበት ወይም ቢጭበረበር የትንሳኤ ቀን እሷ እጅግ በምታስፈልገው ወቅት ላይ ያገኛታል፡፡ ፈንታው ያለምንም ጥርጥር በጣም በሚያስፈልገው ወቅት ላይ እንደሚሰጠው ያወቀ ሰው እንዴትስ ያዝናል? በእርሱና በሞጋቹ መሐከል የሚዳኝውና የሚፈርደው የፍትሃውያን ሁሉ ፍትሃዊ የሆነው ጥበበኛው ዳኛ አላህ(ሰ.ወ) እንደሆነ ያወቀ እንዴትስ ይተክዛል?



በአላህ ውሳኔ (በቀደር) ማመን



በአላህ ውሳኔ የማመን ትርጓሜ



ማንኛውም መልካምም ሆነ መጥፎ ነገር የሚከሰተው በአላህ ውሳኔና ፍርድ እንደሆነ በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ እርሱ ያሻውን ሰሪ ነው፡፡ በእርሱ ፍላጎት እንጂ የሚሆን አንድም ነገር የለም፡፡ ከሱ መሻት የሚወጣ ነገርም የለም፡፡ በዓለም ውስጥ ከርሱ ውሳኔ የሚወጣ ነገር የለም፡፡ ከርሱ ማዘጋጀት ወይም ማስተናበር ባሻገር የሚከሰትም ነገር የለም፡፡ ከዚህም ጋር ትዕዛዛትን እንዲፈፅሙ ባሮቹን አዟል፡፡ ክልከላዎችንም ከልክሏቸዋል፡፡ ለሚሰሯቸው ስራዎቻቸውም የመምረጥ ነጻነት ሰጥቷቸዋል፡፡ አይገደዱም፡፡ ስራቸው የሚከሰተው እንደ ችሎታቸውና እንደ ፍላጎታቸው ነው፡፡ አላህ እነሱንም ችሎታቸውንም የፈጠረ እሱ ነው፡፡ በእዝነቱ ያሻውን ያቀናል፡፡ በጥበቡ ያሻውን ያጠማል፡፡ እርሱ በሚሰራው አይጠየቅም እነርሱ ተጠያቂ ናቸው፡፡


በአላህ ውሳኔ ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ማዕዘን ነው፡፡ ይኸው እውነታ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጂብሪል ሰለ ኢማን ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ ላይ ተዘክሯል፡- « በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በአላህ ውሳኔ በክፉውም በደጉም ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)

በዚህ ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ አንድም ነገር ከአላህ ውሳኔ ውጭ አይሆንም፡፡ .



በአላህ ውሳኔ ማመን ምንን ያካትታል?


በአላህ ውሳኔ ማመን አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካትታል

  • አላህ (ሱ.ወ) በጥቅሉም ሆነ በዝርዝር ስለ ሁሉ ነገር ያውቃል ብሎ ማመን፡፡ እነሆ እርሱ ፍጡራን በሙሉ በርግጥ ከመፈጠራቸው በፊት ያውቃቸዋል፡፡ ሲሳያቸውን፣ ቆይታቸውን፣ ንግግራቸውንና ስራዎቻቸውን አስቀድሞ አውቆታል፡፡ ሁሉንም እንቅስቃሲያቸውንና መርጊያቸውን፣ ሚስጥራቸውንና ይፋቸውን ያውቃል፡፡ ከነርሱ ውስጥ ማናቸው የጀነት ጓዶች እንደሆኑና ማናቸው የእሳት ጓዶች እንደሆኑ አስቀድሞ ያውቃል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱ አላህ ነው፡፡ ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ የኾነ ነው፡፡» (አል ሐሽር 22)
  • አላህ(ሱ.ወ) ተግባራትን ሁሉ አስቀድሞ በለውሕ አል- መሕፉዝ ላይ አስፍሯቸዋል። ስለዚህ ማስረጃ የሚሆነው የሚከተለው አላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው።‹‹ በምድርም በነፍሳችሁም መከራ(ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጂ።ይህ በአላህ ላይ ገር ነው (አል ሐዲድ፡22) ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦‹‹ አላህ የፍጡራንን ችሮታ ሰማያትንና ምድርን ከመፍጠሩ ሃምሳ ሺህ አመታት በፊት ጽፏል።››(ሙስሊም 2653)
  • እርሷን የሚያስተጓጉላት ምንም ነገር በሌላት፣ ተፈጻሚ በሆነችው በአላህ መሻት እና ምንም በማይሳነው በአላህ ችሎታ ማመን፡፡ ማናቸውም ክስተት የሚከሰተው በአላህ መሻትና ችሎታ ነው፡፡ እርሱ የሻው ይሆናል እርሱ ያልሻው አይሆንም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- « የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡» (አል ተክዊር 29)
  • ማናቸውንም ነገር የሚያስገኘውና የሚያስከስተው ወይም የሚፈጥረው አላህ (ሱ.ወ) መሆኑን ማመን፡፡ እርሱ ብቸኛ ፈጣሪ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ ያለ ነገር ሁሉ ፍጡር ነው፡፡ እርሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ነገሩንም ሁሉ የፈጠረውና በትክክልም ያዘጋጀው ነው፡፡» (አል ፉርቃን 2)



የሰው ልጅ ምርጫ፣ ችሎታና ፍላጎት አለው፡፡



በአላህ ውሳኔ ማመን የሰው ልጅ በምርጫው በሚፈጽማቸው ተግባሮቹ ላይ ፍላጎትና ችሎታ አለው ከማለት ጋር አይቃረንም፤ አይጋጭም፡፡ ምክንያቱም የእስላማዊ ድንጋጌና ነባራዊ ተጨባጭ ክስተት ይህንን ለርሱ የሚያረጋግጡና የሚያጸድቁ ናቸው፡፡

ከእስላማዊ ድንጋጌ አንጻር አላህ (ሱ.ወ) መሻትን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- «ይህ የተረጋገጠው ቀን ነው፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መመለስን ይይዛል፡፡» (አል ነበእ 39)

ችሎታን በማስመልከትም አላህ እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡ ለርስዋ የሰራችው አላት፡፡ በርስዋም ላይ ያፈራቺው (ኀጢኣት) አለባት፡፡» (አል በቀራ 286)

ከነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ማንኛውም ሰው ችሎታና መሻት እንዳለውና በነርሱም የሚሰራውን እንደሚሰራ፣ የሚተወውንም እንደሚተው ያውቃል፡፡ እንደመራመድና መሰል እንቅስቃሴዎች ያሉ በፍላጎቱ የሚከሰቱትን፣ እንደመንቀጥቀጥና እንደ ድንገተኛ መውደቅ ያሉ ያለፍላጎቱ ከሚፈጸሙት ለይቶ ያውቃል፡፡ ነገር ግን የፍጡር መሻትና መቻል በአላህ መሻትና ችሎታ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ቀጥተኛ መኾንን ለሻ ሰው (መገሰጫ ነው) ፡፡ የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡» (አል ተክዊር 28-29)

በአንቀጹ ላይ እንደምንመለከተው መጀመሪያ የሰው ልጅን መሻት አጸደቀ፤ ከዚያም በአላህ መሻት ውስጥ የሚካተት እንደሆነ አሳሰበ፡፡ ምክንያቱም ፍጥረተ-ዓለሙ በጠቅላላ የአላህ ይዞታ ነው፡፡ በርሱ ይዞታ ውስጥ ደግሞ ከርሱ ዕወቀትና መሻት ውጭ የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡

> «እኛ ወይ አመስጋኝ ወይም ከሃዲ ሲኾን መንገዱን መራነው (ገለጽንለት)» (አል ደህር 3)



በአላህ ውሳኔ ማመካኘት



የግዳጅና ኃላፊነት፣ የትዕዛዝን የክልከላ ተያያዥነታቸው ከሰው ልጅ ችሎታና ምርጫው ጋር ነው፡፡ አንድ መልካም ሰሪ ቀናውን ጎዳና የመረጠ በመሆኑ ይመነዳል፡፡ መጥፎ ሰሪ ደግሞ እኩይ የሆነን የጥመት መንገድ በመምረጡ ይቀጣል፡፡

አላህ (ሱ.ወ) የምንችለውን እንጂ አላስገደደንም፡፡ በመሆኑም አላህ በርሱ ውሳኔ በማመካኘት እርሱን ማምለክ መተውን ከአንድም ሰው አይቀበልም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሰው ልጅ ከማመጹ በፊት አላህ አውቆ የወሰነው ምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ አላህ ደግሞ ችሎታና የመምረጥ ነጻነት ሰጥቶታል፡፡ የመልካምና የመጥፎን ጎዳና ነጣጥሎ አብራርቶለታል፡፡ በመሆኑም ካመጸ፣ አመጽን ለአላህ ታዛዠ ከመሆን በላጭ አድርጎ የመረጠው እራሱ ነው፡፡ በአመጸኛነቱ የሚያገኘውን ቅጣት የመሸከም ግዴታ አለበት፡፡

> አንድ ሰው በአንተ ላይ ድንበር በማለፍ ንብረትህን ቢውስድብህና ቢያሰቃይህ፣ ከዚያም ለዚህ እኩይ ተግባሩ በርሱ ላይ አላህ የወሰነበት መሆኑን እንደ ምክንያት ቢያቀርብ ምክንያቱ ተቀባይነት አይኖራትም፡፡ በፈጸመው በደል ትቀጣዋለህ፤ ንብረትህንም ታስመልሳለህ፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ይህን የፈጸመው በምርጫውና በፍላጎቱ ስለሆነ ነው፡፡ 


በአላህ ውሳኔ የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ


በአላህ ውሳኔ ማመን በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

1

በአላህ ውሳኔ ማመን በዚህ የሕይወት ቆይታ ንቁ ሆኖ፣ አላህ የሚወደውን በመፈፀሙ እንዲጥርና እንዲተጋ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋነኛውና ትልቁ ነገር ነው፡፡

ምእመናን በአላህ ላይ ከመመካታቸው ጎን ለጎን የክስተት ሰበቦችን እንዲጠቀሙ ታዘዋል፡፡ ኢማን ማለት ደግሞ በአላህ ፍቃድ እንጂ የክስተት ሰበቦች ውጤት ሊያስገኙ እንደማይችሉ እርግጠኛ መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም የክስተት ሰበቦችን የፈጠረው አላህ ነው፡፡ ውጤታቸውንም የፈጠረውም እሱ ነው፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «በሚጠቅምህ ነገር ላይ ታታሪ ሁን፡፡ በአላህ ታገዝ፡፡ አትሳነፍ፡፡ የሆነ (መሰናክል) ነገር ቢገጥምህ እንዲህ እንዲህ ባደረግ ኖሮ እንዲህ እንዲህ ይሆን ነበር አትበል፡፡ ነገር ግን አላህ ወሰነ ያሻውንም ፈፀመ በል፡፡ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ማለት የሸይጣንን በር ትከፍታለች፡፡» (ሙስሊም 2664)

2

የሰው ልጅ የነፍሱን ልክ ማወቅ አለበት፡፡ ሊኮራም ሊኮፈስም አይገባም፡፡ ምክንያቱም እሱ በአላህ የተወሰነውን ነገርና ወደፊት የሚከሰተውን ክስተት ማወቅ የማይችል ደካማ ፍጡር ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ምንጊዜም በደካማነቱና ወደ ፈጣሪው ከጃይ መሆኑን ማመን አለበት፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮው መልካም ነገር ሲገጥመው ይኮራል በርሱም ይታለላል፡፡ መጥፎ ነገርና አደጋ ሲያጋጥመው ደግሞ ይበሳጫል፤ ይተክዛል፡፡ እናም የሰው ልጅን በአላህ ውሳኔ ከማመን በስተቀር መልካም ነገር ሲገጥመው ከመኮፈስና ድንበር ከማለፍ፣ እንዲሁም መጥፎ ነገር ሲገጥመው ከማዘንና ከመተከዝ ሊታደገው የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ማናቸውም የተከሰቱና የሚከሰቱ ነገሮች የአላህ ውሳኔ የተላለፈባቸውና አላህ አስቀድሞ ያወቃቸው ናቸው፡፡

3

በአላህ ውሳኔ ማመን ውግዝ ለሆነው ምቀኝነት እልባት ይሰጣል፡፡ አንድ ሙእሚን አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ሰዎችን አይመቀኝም፡፡ ለነርሱ የለገሳቸውና ይህንን ነገር የወሰነላቸው አላህ (ሱ.ወ) ነው፡፡ እናም ሙእሚን ሌሎችን ሲመቀኝ በአላህ ውሳኔና ፍርድ ላይ እያመጸ መሆኑን ወይም ውሳኔውን እየተቃወመ እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም አይመቀኝም፡፡

4

በአላህ ውሳኔ ማመን በልብ ውስጥ ችግሮችን ለመጋፈጥ ጀግንነትን ይፈጥራል፡፡ ቁርጠኝነትንም ያጠናክራል፡፡ ምክንያቱ፣ በአላህ ውሳኔ ማመን የዱንያ ቆይታ (አጀል) ሲሳይ በአላህ የተወሰነ እንደሆነና የሰው ልጅን የሚያጋጥመው የተጻፈው ነገር ብቻ መሆኑን እርግጠኛ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ነው፡፡

5

በአላህ ውሳኔ ማመን በሙእሚን ነፍስ ውስጥ የተለያዩ የኢማን ጭብጦችን ይተክላል፡፡ እርሱ ምንጊዜም እገዛ የሚሻው ከአላህ ብቻ ነው፡፡ የክስተት ሰበቦችን ከመፈፀሙም ጋር የሚንተራሰውና የሚመካው በአላህ ላይ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ምንጊዜም ጌታውን ከጃይ ይሆናል፡፡ በጽናት ላይ እንዲያበረታው ከርሱ እገዛን ይፈልጋል፡፡

6

በአላህ ውሳኔ ማመን የመንፈስ እርጋታን ይፈጥራል፡፡ ሙእሚን፣፣ የደረሰበት ነገር መጀመሪያውኑ ሊስተው እንዳልነበረ፣ የሳተውም ነገር መጀመሪያውኑ ሊያገኘው እንዳልነበረ ያውቃል፡፡