በእስልምና ሃይማኖት በጌታና በባሪያው መሃል አማላጅ የለም፡-

በእስልምና ሃይማኖት በጌታና በባሪያው መሃል አማላጅ የለም፡-


ብዙ ሃይማኖቶች ለአንዳንድ ግለሰቦች ከሌላው ሰው በተለየ መልኩ ሃይማኖታዊ መለያዎችን ችረዋል፡፡ የሰዎች የአምልኮ ጥንካሬም ሆነ የእምነት ደረጃ የሚለካው በእነዚህ ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እንዲሆን አድርገዋል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች በእነዚህ ሃይማኖቶች መሠረት በሰውና በአምላክ መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አገናኝ ድልድዮች መሆናቸው ነው፡፡ ምህረት የሚለግሱትም እነርሱ ናቸው፡፡ የሩቅ ምስጢር (ገይብ) አዋቂ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ይህ እነርሱን ግልፅ ኪሳራ ላይ የጣላቸው የሃቅ ተቃራኒ የሆነና የሐሰት ጥሪያቸው ነው፡፡

በእስልምና ሃይማኖት በጌታና በባሪያው መሃል አማላጅ የለም፡-

ነገርግን ኢስላም ብርሃኑን ፈነጠቀና ለሰው ልጅ ክብርን አጎናፀፈው፣ ከፍ ያለ ደረጃም ሰጠው፡፡ የሰው ደስታ፣ ንሰሐም ሆነ አምልኮ መወሰን ያለበት የፈለገውን ያህል ክብርና ደረጃ ይኑራቸው በጥቂት ግለሰቦች ፈቃደኝነት ላይ ነው የሚለውን ከንቱ አስተሳሰብ ውድቅ አደረገው፡፡

የአንድ ሙስሊም የአምልኮ ተግባር የሚወሰነው በርሱና በአላህ መካከል ብቻ ነው፡፡ ሌላ በመሃከል ሆና የሚያገናኝ አማላጅ ግለሰብ አያስፈልግም፡፡ አላህ ለባሪያው ቅርብ የሆነ ጌታ ነው፡፡ የባሪያውን ጥሪ ሰምቶ ምላሽ መስጠት ይችላል፡፡ አምልኮውን፣ ሶላቱን በመመልከትም ምንዳ ይሰጠዋል፡፡

ማንኛውም የሰው ዘር ምህረት የመቸርም ሆነ ንሰሀ የመቀበል መብትም ሆነ ሥልጣን የለውም፡፡ አንድ የአላህ ባሪያ የሆነ ግለሰብ ለአላህ ፍፁም ቅን ሆኖ ንሰሃ እስከገባ ድረስ፥ አላህ ንሰሀውን ይቀበለዋል ምህረትም ይለግሰዋል፡፡ ማንም ግለሰብ በዚህ ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ ተፅዕኖ የማሳደር መለኮታዊ ኃይል የለውም፡፡ ነገራት ሁሉ የሚከናወኑት በአላህ እጅ ነው፡፡

የእስልምና ሃይማኖት የሙስሊም አዕምሮ ነፃ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በጥልቅ እንዲያዝና እንዲመራመር ጥሪ አቅርቦለታል፡፡ በአንድ ጉዳይ ሲወዘገብም በቁርዓንና በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የተረጋገጠ ንግግርና ተግባር እንዲዳኝ አዞታል፡፡

ከአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በስተቀር ለማንኛውም ሰው በሚናገረው ንግግር ሁሉ ሰዎች ለርሱ ፍፁም ታዛዦች እንዲሆኑለት የማድረግ ስልጣን የለውም፡፡ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ.) ግን ከአላህ በሆነ ወህይ (በራዕይ) እገዛ ካልሆነ ከራሳቸው አፍልቀው የሚናገሩት አንዳችም ነገር ስለሌለ እርሳቸውን ያለምንም ማወላዳት መታዘዙ ተገቢ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል …«ከልብ ወለድም አይናገርም፡፡ እርሱ (ንግግሩ) የሚወረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡» (አል-ነጅም፡3-4)

አላህ በዚህ ሃይማኖት አማካኝነት ምን ያህል ታላቅ ፀጋ እንዳጎናፀፈን እናስተውል! ሃይማኖቱ ከአፈጣጠራችን ጋር ተስማሚ ነው፡፡ የሰውን ክቡርነት ይጠብቃል፡፡ ሰው ራሱን በራሱ ብቻ የሚገዛና ከአላህ ውጪ የማንም ተገዢና ባሪያ እንዳይሆን ነፃ ያወጣል፡፡