ኢስላም ዘካ የሚሰጣቸውን ክፍሎች ገድቦ አስቀምጧል፡፡ አንድ ሙስሊም ከነኚህ ክፍሎች መካከል ለአንዱ ብቻ ወይም ከአንድ በላይ ለሆኑ አካሎች ዘካውን መስጠት ይችላል፡፡ ለሚገባቸው ክፍሎች ሊያከፋፍሉለት ለሚችሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበሮች መስጠትም ይችላል፡፡ ዘካን በሀገር ውስጥ ማከፋፈሉ በላጭ ነው፡፡
ዘካ የሚገባቸው ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡
1
ድሆችና ችግረኞች፡ አንገብጋቢና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላትና ለመሸፈን በቂ አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡
2
ዘካን በመሰብሰብና በማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማሩ የዘካ ሰራተኞች
3
ከአሳዳሪው እራሱን በመግዛት ነፃ ለመውጣት ለሚጥር ባሪያ፡፡ ይህ ሰው ዘካን በመውሰድ ነፃነቱን ያውጃል፡፡
4
ብድር ተበድሮ መክፈል ያቃተው ሰው፡ የተበደረው ብድር ለሰዎች በጎ ለመዋልና ለሕዝባዊ ጥቅም ወይም ለግል ጉዳይ ቢሆንም ልዩነት አይኖረውም፡፡
5
በጦር ግንባር በአላህ መንገድ ላይ ለሚፋለም ጀግና፡ እነኚህ ደግሞ ከሃይማኖታቸውና ከአገራቸው ጠላትን በመመከትና በመጋፈጥ ላይ ያሉ ተዋጊዎች ሲሆኑ ማንኛውም ኢስላምን ለማስፋፋትና ለማሰራጨት፣ የአላህን ቃል ከፍ ለማድረግ የሚሰራ ስራም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡
6
ልቦናቸው ከኢስላም ጋር በመላመድ ላይ ላሉ አዲስ ሙስሊሞች፡ እነኚህ፣ ከሃዲያን የነበሩ፣ በቅርቡ ኢስላምን የተቀበሉ፣ ወይም ይሰልማሉ ተብሎ የሚከጀሉና ተስፋ የሚጣልባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለእነኚህ ዘካ የሚሰጧቸው ግለሰቦች ሳይሆኑ፣ መንግሳታዊ ክፍሎችና ጠቃሚነቱን ሊያገናዝቡና ሊመረምሩ የሚችሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ናቸው፡፡
7
ስንቅ ያለቀበት መንገደኛ፡ ይህ ሰው በአገሩ ከፍተኛ ካፒታል ወይም ንብረት ያለው ቢሆንም ባለበት ሁኔታ፣ ስንቅ ካለቀበት፣ ከተቋረጠበትና ገንዘብ ካስፈለገው ዘካ ይሰጠዋል፡፡
አላህ (ሱ.ወ) ዘካ የሚገባቸውን ክፍሎች ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድሆች፣ ለሚስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በኢስላም) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም ነፃ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሰሩ፣ በመንገደኞችም ብቻ ነው፡፡›› (አል ተውባ 60)

ድሆች ማለት ለአስፈላጊና መሠረታዊ ፍላጐቶችን የሚያሟሉበት አቅም የሌላቸው ማለት ነው።
የእንሰሳት ሃብት ዘካ
የእንሰሳት ሃብት፣ሰዎች የሚገለገሉባቸው የቤት እንሰሳት ማለት ነው፡፡ እነሱም ግመል፣ ላምና ፍየል ወይንም በግ ናቸው፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እነኚህን እንሰሳት በመፍጠር ለሰዎች ትልቅ ውለታ ውሎላቸዋል፡፡ ሰዎች ስጋዎቻቸውን ይመገባሉ፤ ከቆዳዎቻቸው ልብስን ይለብሳሉ፤ በመንገድ ሲጓዙና ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እነሱንና ጓዛቸውን ይሸከሙላቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ግመልን፣ ከብትን፣ ፍየልንም፣ በርሷ (ብርድን መከላከያ) ሙቀት፣ ጥቅሞችም ያሉባት ስትኾን ለናንተ ፈጠረላችሁ ከርሷም ትበላላችሁ፡፡ ለናንተም በርሷ ወደ ማረፊያዋ በምትመልሷት ጊዜ፣ በምታሰማሩዋትም ጊዜ ውበት አላችሁ፡፡ ጓዞቻችሁንም በነፍሶች ችግር እንጂ ወደማትደርሱባት አገር ትሸከማለች ጌታችሁ በእርግጥ ርኀሩኅ አዛኝ ነውና፡፡ (አል ነሕል 5-7)
የእንሰሳት ዘካ ጥቅላዊ መስፈርቶች
በእነኚህ እንሰሳት ላይ ዘካ ግዴታ የሚሆነው የሚከተሉት መስፈርቶች ሲሟሉ ነው፡
1
ብዛታቸው የኢስላማዊውን ዘካ የማውጫ መጠን(ሂሣብ) መድረስ፡ ምክንያቱም ዘካ በባለሃብቶች ላይ እንጂ በሌላው ላይ ግዴታ አይደለም፡፡ ለግል ጉዳያቸው የሚጠቀሙባቸው ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ እንሰሳት ያሉት ሰው የዘካ ግዴታ የለበትም፡፡ ከግመል ዘካ የሚወጣው ቁጥራቸው አምስት ሲደርስ ነው፡፡ ለፍየል አርባ፣ ለላም ደግሞ ሰላሳ ነው፡፡ ቁጥራቸው ከዚህ ቁጥር በታች ከሆነ የዘካ ግዴታ የለበትም፡፡
2
በይዞታነት ባለሀብቱ ዘንድ አንድ ሙሉዕ የጨረቃ ዓመት ሊዞርባቸው ወይም ሊያስቆጥሩ ይገባል፡፡
3
በግጦሽ ላይ ተሰማርተው የሚበሉ መሆን አለባቸው፡ እንሰሰዎቹ በግጦሽ ላይ የሚኖሩ፣ ድርቆሽና ግጦሽ በማቅረብ ባለንብረቱ ወጪ የማያደርግባቸው መሆን አለበት፡፡
4
እንሰሳቱ በስራ የተጠመዱ መሆን የለበትም፡፡ ባለቤቱ ማሳውን የሚያርስበት ወይም ዕቃ የሚያጓጉዝበት ወይም እራሱ የሚጓጓዝበት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ከሆነ ዘካ የማውጣት ግዳጅ የለበትም፡፡

የጋማ ከብቶች የዘካ አወጣጥ
1
ግመል
ሁሉም የግመል ዓይነቶች ባለ አንድ ሻኛ ወይም ባለ ሁለት ሻኛ ቢሆኑም ብዛታቸው አምስት ከደረሰ ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው፡፡
ብዛት | ግዴታ የሚሆንበት መጠን | |
ከ | እስከ | |
5 | 9 | አንድ ሴት ፍየል |
10 | 14 | ሁለት ሴት ፍየሎች |
15 | 19 | ሦስት ሴት ፍየሎች |
20 | 24 | አራት ሴት ፍየሎች |
25 | 35 | ቢንት መኻድ (የአንድ ዓመት እድሜዋን ጨርሳ ሁለተኛ ዓመት እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል) |
36 | 45 | ቢንት ለቡን (የሁለት ዓመት እድሜዋን ጨርሳ ሦስተኛ እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል) |
ብዛት | ግዴታ የሚሆንበት መጠን | |
ከ | እስከ | |
46 | 60 | ሒቃህ (የሦስት ዓመት እድሜዋን ጨርሳ አራተኛ እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል) |
61 | 75 | ጀዝዐህ (የአራት ዓመት እድሜዋን ጨርሳ አምስተኛ እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል) |
76 | 90 | ሁለት ቢንት ለቡን (የሁለት ዓመት እድሜያቸውን ጨርሰው የሦስተኛ ዓመት እድሜያቸውን የጀመሩ ሴት ግመሎች) |
91 | 120 | ሁለት ሒቃህ (የሦስተኛ ዓመት እድሜያቸውን ጨርሰው የአራተኛ ዓመት እድሜያቸውን የጀመሩ ሴት ግመሎች) |
ብዛታቸው ከ120 በላይ ሲሆን በየ40ዎቹ ተጨማሪ ግመሎች | አንድ ቢንት ለቡን (የሁለት ዓመት እድሜዋን ጨርሳ የሦስተኛ ዓመት እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል) ከላይ ከተቀመጠው ቁጥር ላይ ይጨመራል፡፡ | |
በየ50ዎቹ ተጨማሪ ግመሎች | አንድ ሒቃህ የሦስተኛ ዓመት እድሜዋን ጨርሳ የአራተኛ ዓመት እድሜዋን የጀመረች ሴት ግመል ከበላይ ከተቀመጠው ቁጥር ላይ ይጨመራል |

2
ከብት
ከከብት ላይ ዘካ ግዴታ የሚሆነው የከብቶቹ ቁጥር ከ30 በላይ ሲሆን ነው
ብዛት | ግዴታ የሚሆንበት መጠን | |
ከ | እስከ | |
30 | 39 | አንድ ጥጃ (አንድ ዓመት የሞላው ጥጃ) |
40 | 49 | አንድ ሙሲናህ (የሁለት ዓመት እድሜዋን የጨረሰች ላም) |
60 | 69 | ሁለት ጥጆች (ሁለት ዓመት የሞላቸው) |
70 | 79 | አንድ መሲናህ (ሁለት ዓመት የሞላት ላም) እና ተቢዕ (አንድ ዓመት የሞላው ጥጃ) |
80እና ከዚያ በላይ በየ30ዎቹ | አንድ ተቢዕ (አንድ ዓመት የሞላው ጥጃ) ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር ላይ ይጨመራል፡፡ | |
በየ40ዎቹ | ሙሲናህ (ሁለት ዓመት የሞላት ላም) ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር ላይ ይጨመራል፡፡ |

3
በግና ፍየል
የበጎችና የፍየሎች ቁጥር ከ40 በላይ ሲሆን ዘካ ማውጣት ግዴታ ይሆናል

ብዛት | ግዴታ የሚሆንበት መጠን | |
ከ | እስከ | |
40 | 120 | አንድ በግ (ፍየል) |
121 | 200 | ሁለት በግ (ፍየል) |
201 | 399 | ሦስት በግ (ፍየል) |
400 | 499 | አራት በግ (ፍየል) |
500 | 599 | አምስት በግ (ፍየል) |
ከ600 በላይ ከሆነ በእያንዳንዱ 100 ተጨማሪ በግና ፍየል አንድ በግ ወይም ፍየል ተጨማሪ ይደረጋል | ||
600 | 6 በግ (ፍየል) | |
700 | ሰባት በግ (ፍየል) |
የአዝርዕትና የጥራጥሬዎች ዘካ
የአዝርዕትና የጥራጥሬዎች ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው መስፈርቶች፡-
1
ምርቱ የዘካ ማውጫ መጠን (ሂሣብ) የደረሰ መሆኑ
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘካ ማውጣት ግዳጅ የሚሆንበትንና ከርሱ በታች ከሆነ ዘካ ማውጣት ግዳጅ የማይሆንበትን መጠን (ሂሳብ) ወሰን አበጅተውለታል፡፡ ይህንኑ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከአምስት አውሱቅ በታች የሆነ የተምር ምርት፣ የዘካ ግዳጅ የለበትም፡፡›› (አል ቡኻሪ 1405 / ሙስሊም 979)
አውሱቅ ማለት የስፍር መለኪያ ሲሆን፣ ከ580 እስከ 600 ኪሎግራም የሚደርስ የስንዴና የሩዝ መጠንን ይመዝናል፡፡ ስለዚህም፣ መጠኑ ከዚህ በታች በሆነ ፍሬ ላይ ዘካ ግዴታ አይሆንም፡፡
2
አዝርዕቶቹ ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው የአዝርዕት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
የሰው ልጅ እንደምግብነት በምርጫው የሚጠቀምባቸውና በክምችት መልክ ለረዥም ጊዜ ሳይበላሹ ሊቀመጡ የሚችሉ፣ እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘቢብ፣ ተምር፣ ሩዝና በቆሎ የመሳሰሉ አዝርዕቶች ናቸው፡፡
ለመሰረታዊ ምግብነት የማያገለግሉና ሳይበላሹ፣ ሊከማቹ የማይችሉ የሆኑ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ላይ የዘካ ግዴታ የለም፡፡ እንደ ሩማን፣ እቾሎኒና የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡
3
ምርቱ ሙሉ ለሙሉ የተሰበሰበ ወይም የተለቀመ መሆን አለበት
በአዝርዕትና በጥራጥሬዎች ላይ ዘካ ግዴታ የሚሆነው ምርቱ ሙሉ ለሙሉ ከተሰበሰበና ከተለቀመ በኋላ ነው፡፡ ዓመት መቆጠሩ መስፈርት አይሆንም፡፡ ምርቱ በተሰበሰበበት ወቅት የሚፈፀም ይሆናል፡፡ በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ምርቱ የሚሰበሰብ ከሆነም በእያንዳንዱ የምርት ለቀማ ወቅት ዘካ ማውጣት ግዴታ ይሆናል፡፡ በዚሁ መልክ በየ ምርት ለቀማ ወቅት ዘካ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ዘካ አውጥቶለት ለረዥም ዓመታት ቢያከማቸው በዚያ ክምችቱ ላይ ዘካ የማውጣት ግዴታ የለበትም፡፡
ግዴታ የሚሆነው የዘካ መጠን
ኢስላም፣ በዝናብና በወንዝ በሚለሙ የአዝርዕት ምርቶችና በሰው ጉልበት ወይም በመስኖ የሚለሙ የአዝርዕት ምርቶች መካከል የሚወጣውን የዘካ መጠን አበላልጧል፡፡ በዝናብና በወንዝ የሚለሙ የአዝርዕት ምርቶች ላይ ዐሥር በመቶ
እንዲወጣ፣እንዲሁም ገበሬው በመዝራቱ፣ በማጠጣቱና ውሃ ወደ ማሳው እንዲደርስ በማድረጉ፣ ከምንጭና ከጉርጎድ ውሃ በማውጣት መስኖ በማዘጋጀት ለፍቶና ደክሞ ያመረታቸውን ደግሞ አምስት በመቶ ዘካ እንዲያወጣ አዟል፡፡
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ዝናብና ምንጮች ባጠጧቸው ምርቶች ላይ አንድ አስረኛ፣ በመስኖ በጠጡ ምርቶች ላይ ደግሞ የአንድ አስረኛ ግማሽ ዘካ አለበት፡፡›› (አል ቡኻሪ 1483)
