ቤተሰብ በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ

ቤተሰብ በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ


የሚከተሉት ጉዳዮች ኢስላም ለቤተሰብ ልዩ እንክብካቤና እገዛ ማድረጉን በግልጽ ያሳያሉ፡-

1

ኢስላም በጋብቻ ጅማሬና በቤተሰብ ምስረታ ላይ ልዩ እይታ አለው፡፡ በመሆኑም ከስራዎች ሁሉ የላቀ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር፣ የመልክተኞች ፈለግ እንዲሆንም አድርጎታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ነገር ግን እኔ እጾማለሁ እፈታለሁም፤ እሰግዳለሁ አሸልባለሁም፤ ሴትም አገባለሁ፡፡ ከኔ ፈለግ የወጣ ከኔ አይደለም፡፡››

(አል ቡኻሪ 4776 /ሙስሊም 1401)

  • ቁርኣን ከታላላቅ ተዓምራትና ጸጋዎች ጎራ ከቆጠራቸው ነገሮች አንዱ አላህ (ሱ.ወ) በባልና ሚስት መሐከል ፍቅርን እዝነትንና እርካታን ማድረጉን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለናንተም ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ታምራቶች አልሉ፡፡›› (አል ሩም 21)
  • ጋብቻን ገር ማድረግ፣ ለማግባት የሚፈልግም ሰው ነፍሱን ከዝሙት እንዲጠብቅ መረዳትና መታገዝ እንዳለበት ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ ሦስት ዓይነት ሰዎችን ለመርዳትና ለማገዝ በራሱ ላይ ግዴታ አድርጓል፡፡›› አሉና ከነሱ መካከል፣ ‹‹ጥብቅነትን ፈልጎ ጋብቻን የፈፀመን ሰው›› ጠቅሰዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 1655)
  • ወጣቶችን ገና በአፍላ ዕድሚያቸውና ባልተነካ ጉልበታቸው ላይ ሳሉ ጋብቻን እንዲፈፅሙ አዟል፡፡ ምክንያቱም ጋብቻ ለነሱ መርጊያቸውና መርኪያቸው ስለሆነ ነው፡፡ ለፍቶት ስሜታቸውና ፍላጎታቸው ትክክለኛ መፍትሄም ነው፡፡

ቁርኣን በባልና በሚስት መሐከል ያለን እርካታ፣ ፍቅርና መተዛዘን ከታላላቅ ጸጋዎች መድቦታል፡፡  

2

ኢስላም ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ወንድም ሆነ ሴት ልዩ ክብር ሰጥቷል፡፡

ኢስላም ልጆችን የመንከባከብና በማሳዳግ ጉዳይ በእናትና በአባት ላይ ከባድ ኃላፊነት ጥሏል፡፡ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ ማለታቸው ተላልፏል፡- ‹‹ሁላችሁም እረኞች ናችሁ፤ ማናችሁም ከሚጠብቀው ይጠየቃል፡፡ አንድ መሪ እረኛ ነው፤ በጥበቃው ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ አባወራ በቤተሰቡ ላይ እረኛ ነው፤ በርሱ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ ሴትም በባሏ ቤት ውስጥ እረኛ ነች፤ በርሷ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነች፡፡ ባሪያ በአሳዳሪው ንብረት ላይ እረኛ ነው፡፡ በርሱ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 853 /ሙስሊም 1829)

3

ኢስላም ለአባቶችና ለእናቶች ክብር በመስጠትና ደረጃቸውን በመጠበቅ፣ እንዲሁም እስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ድረስ እነርሱን መንከባከብና ትዕዛዛቸውን መፈፀምን አስመልክቶ ልዩ ትኩረት ቸሯል፡፡

ወንድ ወይም ሴት ልጅ፣ ምንም ያህል ትልቅ ሰው ቢሆኑም ለወላጆቻቸው ታዛዥ የመሆንና ለነሱ በጎ የመዋል ግዴታ አለባቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ጉዳይ ከርሱ አምልኮ ጋር አቆራኝቶ ጠቅሶታል፡፡ እነርሱ ላይ በንግግርና በተግባር ድንበር ማለፍን ከልክሏል፡፡ በነሱ መናደዱን የሚመለክትን ቃል ወይም ድምፅ ማሰማትንም ሳይቀር ከልክሏል፡፡ ‹‹ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ፤ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡›› (አል ኢስራእ 23)

4

ኢስላም የወንድም ሆነ የሴት ልጆችን መብት እንድንጠብቅ አዟል፡፡ በመካከላቸው በወጪም ሆነ በይፋ በሚታዩ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊ መሆንም ግዴታ ነው፡፡

5

ኢስላም በአንድ ሙስሊም ላይ ዝምድናን የመቀጠል ግዴታ ጥሎበታል፡፡ ይህ ማለት በእናቱም ሆነ በአባቱ በኩል ያሉትን ዘመዶቹን ዝምድና በመቀጠልና ለነርሱ በጎ በመዋል ይገለፃል፡፡

ወንድሞቹ፣ እህቶቹ፣ አጎቶቹ፣ አክስቶቹና ልጆቻቸው እዚህ ውስጥ የሚገቡ ሲሆን ለነርሱ መልካም መስራት፣ ከታላላቅ ወደ አላህ መቃረቢያዎችና ታዛዥነትን መግለጫ መንገዶች መካከል ቆጥሮታል፡፡ ዝምድናቸውን ከመቁረጥ፣ ወይም ክፉ ነገር በነርሱ ላይ ከመፈፀም እንድንርቅ አስጠንቅቋል፡፡ ይህን ማድረግን ከከባባድ ወንጀሎች ፈርጆታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ዝምድናን ቆራጭ ጀነት አይገባም፡፡›› (አል ቡኻሪ 5638 /ሙስሊም 2556)

ኢስላም ለእናትና ለአባት ክብር የመስጠትን መሰረት ጥሏል፡፡