ልብስ በኢስላም

ልብስ በኢስላም


አንድ ሙእሚን ከሰዎች ጋር ለመደባለቅና ሠላትን ለመስገድ የሚለብሰው ልብስ፣ የሚያምርና ንጹህ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ (ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡›› (አል አዕራፍ 31)


አላህ (ሱ.ወ)፣ የሰው ልጅ በአለባበሱና በይፋዊ መገለጫው እንዲቆነጃጅ የሚያዘው ሕግን ደንግጓል፡፡ ይህ በራሱ የአላህን ጸጋ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአላህን ጌጥ ያችን ለባሮቹ የፈጠራትን ከሲሳይም ጥሩዎቹን እርም ያደረገ ማን ነው? በላቸው እርሷ በትንሳኤ ቀን ለነዚያ ላመኑት ብቻ ስትኾን በቅርቢቱ ሕይወት ተገቢያቸው ናት፡፡ በላቸው እንደዚሁ ለሚያውቁ ሕዝቦቹ አንቀጾችን እናብራራለን፡፡›› (አል አዕራፍ 32)


ልብስ ብዙ ጉዳዮች ይፈጸሙበታል፡


1

የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ከእይታ ይሸፍናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን፡፡›› (አል አዕራፍ 26)

2

ገላን ከሙቀትና ከውርጭ፣ እንዲሁም ከጎጂ ነገሮች ይጠብቃል፡፡

ብርድና ሙቀት ተለዋዋጭ የአየር ንብረቶች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ የልብስን ገጽታ በማስመልከት እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሐሩርንም (ብርድንም) የሚጠብቋችሁን ልብሶች፣ የጦራችሁንም አደጋ የሚጠብቋችሁን ጥሩሮች ለናንተ አደረገላችሁ፡፡እንደዚሁ ትሰልሙ ዘንድ ጸጋውን በናንተ ላይ ይሞላል፡፡›› (አል ነሕል 81)